የሀገር ውስጥ ዜና

ትልቅ ሀገር – ትልቅ ሕዝብ – ታላቅ ርዕይ

By betelhem girma

September 28, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከትላንት እንማራለን፤ ዛሬን እንሰራለን ነገን የተሻለ እናደርጋለን። ይህንን ንግግር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ይህ ከትናንት የመማር፣ ዛሬን የመትጋትና የተሻለ ነገን የማኖር ሀሳብ እንደ ቀላል የሚወሰድ ሳይሆን ይልቁን የኢትዮጵያን ታላቅነት ለማስቀጠል የሚተጋ ሁሉ ሊመራበት የሚገባ አካሄድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ትናንቷ ብዙ የሚያስተምር የከፍታ ታሪክ ያላት ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነች ታላቅ ሀገር ነች፡፡ በታሪክ፣ በባሕልና በተፈጥሮ ሀብት ሁሉ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ልትጠቀስም የምትችል ናት፡፡

ያለፉት ዘመናት ግን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዋ ከትናንት የኩራት ታሪኳ ጋር አልጣጣም ብሎ ትውልዱ የሚወቀስበት አባቶቹን አይመስልም በሚባልበት የኩስመና ዘመን ይገለፃሉ፡፡

በዚህም ትውልዱ ታላቅ ነበርን ታላቅም እንሆናለን ሲል በትናንት የታላቅነት ታሪክና በነገ ታላቅ የመሆን ተስፋ መሐል ይዋልል ነበር፡፡

ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ይህን ለወቀሳ የዳረጋትን ዘመን ሽራ ታላቅ ነበርን፣ ታላቅ ነን፣ ነገም ታላቅ እንሆናለን ስትል በተግባር አስደግፋ የከፍታና የማንሠራራት ጉዞዋ ላይ ትገኛለች፡፡

የአባቶቹን አልበገር ባይነትና ትጋት የወረሰው ትውልድም ዛሬንም ኢትዮጵያን በሚገባት ቁመና ላይ ለማቆም እየተጋ ይገኛል፡፡

ከትናንት አባቶቹ ስህተት ተምሮ፣ በጎ ነገራቸውን ወስዶና አሳድጎ ዛሬን በተገባና በተሻለ መንገድ ሰርቶ የኢትዮጵያን ታላቅነት ማስቀጠሉን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡

እንደ አክሱም፣ ላሊበላ፣ የፋሲል ግንብ፣ የባሌ ሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግሥት በሕብረት ሲገነባና ለውጤት ሲያበቃ የሚታወቀውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ዛሬም ሕዝቡ ዳግማዊ ዓድዋ በሆነው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ማስቀጠል ችሏል፡፡

በተጨማሪም በሀገሪቱ በተካሄደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ከትናንት ተከትለው የዘለቁ ለቁርሾና ስብራት ምክንያት የሆኑብንን ችግሮች ዛሬ ላይ በውይይት አክሞ ነገን በተሻለና በጋራ ስምምነት ላይ የሚፀና ሀገረ መንግሥትን ለመመስረት የተደረገ ፍሬያማ ተግባር ነው፡፡

ዛሬም ኢትዮጵያ ሁሉ የሚመሰክርላት ታላቅ ሀገር ናት፤ ነገር ግን ታላቅነቷ እንደፀና የምትቆየው ከሕዝብ ታላቅነት ባሻገር ነገዋን ካለመችበት የሚያደርሳት ታላቅ ራዕይ ያስፈልጋታል፡፡

ለሀገር የሚበጃትን ታላቅ ራዕይን የሰነቀ ፣ ይህንንም ራዕይ በቃል ብቻ ተወርቶ እንዳይቀር ወደ ተግባር ለመቀየርና ከግብ ለማድረስ የሚያስችል የአመራርነት ጥበብን የተላበሰ መንግሥትም ትሻለች፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ታላቅነቷን አስጠብቃ፣ ወደ ከፍታ የሚያደርሳትን ታላቁን ራዕይ ሰንቃ የመተባበርና የመትጋት ማንነት ባላቸው ታላቅ ሕዝቦቿ በተግባር ነገዋን እየሰራች ትገኛለች፡፡

በቤተልሔም ግርማ