የሀገር ውስጥ ዜና

የባሕር በር የትውልዱ ታሪካዊ ምዕራፍ – ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ራዕይ

By tigist gizachew

September 29, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪካዊ ጠላቶቿንና የቅኝ ግዛት ወራሪዎችን ድል ካደረገችበት ታሪኳ ጀምሮ፣ የአፍሪካን ትልቅ የውኃ ግድብ በራሷ አቅም የገነባችው ኢትዮጵያ በትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ያላትን የመፈጸም ቁርጠኝነት አሳይታለች።

ኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን በማጠናከርና ከጎረቤቶቿ ጋር የሚበጀውን ሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ በመከተል፣ ዓባይን የማልማትና ባሕር የመንካት ህልሟን ማሳካቷ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ ከዓባይ እስከ ባህር በር ያላትን ህጋዊና ታሪካዊ ጥቅም ለማስከበር የምታደርገው ጥረት ፍትሃዊ በመሆኑ፣ የህዝቧ አንድነትና ቁርጠኝነት ካለ የሚያደናቅፋት ኃይል አይኖርም።

ይህ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የሉዓላዊነት መብት እንዲሁም ወደ ባሕር በር (ቀይ ባሕር) ለመድረስ የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጥረት የሚያንፀባርቅ ታላቅ ራዕይ ነው።

ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር በጠበቀ ትስስር አብረው እንዲያድጉ እና የጋራ ብልጽግናን እንዲያረጋግጡ የተዘረጋው እጅ ሰላማዊ እና ህጋዊ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን የተከተለ ነው።

ኢትዮጵያ ጠንካራ እና ራሷን የቻለች ሀገር ሆና እንድትወጣ የማይፈልጉ ጠላቶች ፍትሐዊውን የባሕር በር ጥያቄዋን ለማጣጣል ይሞክራሉ።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚፈጠሩ የትብብር በሮችን ለመዝጋት የፕሮፓጋንዳ እና የፖለቲካ ጫናዎችን ለማብዛት ቢፍጨረጩሩም፣ የኢትዮጵያን ፍትሐዊ ጥያቄና የልማት ግስጋሴ ግን ለመግታት አቅም ያላቸው አይደሉም።

ቀይ ባሕር በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ፣ በባሕር ላይ ውንብድና፣ በህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም በጽንፈኝነት ስጋቶች የሚታመስ ቀጣና ነው፡፡

እነዚህን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ለመከላከል ትልቅ ሕዝብ እና ታላቅ ራዕይ ያላት ኢትዮጵያ በቀጣናው መገኘቷ፣ ለቀጣናው አስተማማኝ ጸጥታ ለመስጠት ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡

በመሆኑም የወደፊቱ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዕድገትና መረጋጋትም በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጥንካሬና ብልጽግና ጋር የተያያዘ በመሆኑ የመደመር መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ያደረገው የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ከኢኮኖሚ ነፃነት ባለፈ ቀጣናዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መስፋፋት አስተማማኝ የባሕር በር መዳረሻ የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ወቅት ለገቢና ወጪ ንግዷ ከወደብ ጋር በተያያዘ ያለባት ችግር ተወዳዳሪነቷ እንዲጎዳ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ማሳካትም እንደምትችል ማሳየት የቻለው የመደመር መንግሥት የዚህ ትውልድ የባሕር በር ፍላጎት ምላሽ እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ መጪው ትውልድ የጸናች ሀገር እንዲረከብ ያስችላል።

በትዕግስት ግዛቸው