አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ፍትሃዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን በዲፕሎማሲ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ በመመስረት እውን ለማድረግ የያዘው ጽኑ አቋም ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን እያጎናጸፈው ይገኛል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ በየትኛውም መስፈርት የሀገርና የሕዝብን ሕልውና መሠረት ያደረገ የፍትሕ ጥያቄ ነው።
በአፍሪካ በፈጣን ዕድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የንግድ ልውውጥ እና ከሕዝብ ቁጥር ማደግ ጋር ተያይዞ የባሕር በር ማግኘት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጥያቄም ጭምር ሆኗል።
በታሪክ የኢትዮጵያና የቀይ ባሕር ቁርኝት ትናንት የተወለደ የፖለቲካ ፈጠራ ሳይሆን የሺህ ዓመታት ዕድሜ ያለው የባህልና የንግድ ድልድይ ነው።
አክሱም እና ሌሎች ቀደምት የኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች እንደ አዱሊስ ያሉ ታላላቅ ወደቦችን በመጠቀም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።
ይሁን እንጂ በታሪክ በተፈጠረ ሴራ ኢትዮጵያ ከባሕር በር ባለቤትነት እንድትርቅ መደረጓ በምጣኔ ሃብቷና በደህንነቷ ላይ ከባድ ጫና ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ በሴራ ወደብ አልባ መደረጓን ተከትሎ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ እና አገልግሎት በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ክፍያ እንድትከፍድ ተገድዳለች።
በተለይም የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት የሚመለከቱ ከውጭ የምታስገባቸው ሚስጢራዊ ዕቃዎች በሌላ ሀገር ይሁንታ ሥር መውደቃቸው ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።
ይህ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነት በእጅጉ የሚገታ ሲሆን÷ ባሕር በር ለኢትዮጵያ የንግድ ማሳለጫ ብቻ ሳይሆን የብሔራዊ ደህንነትና የጂኦፖለቲካዊ ሚዛን መጠበቂያ ቁልፍ መሳሪያ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የተፈጥሮና የታሪክ ፍትሕን በሰላማዊ መንገድ የመጠየቅ ሕጋዊ ጉዞ ነው።
በምስራቅ አፍሪካ የሕዝብ ብዛት፣ የሰላም አስከባሪ ኃይል አስተዋጽኦ እና የኢኮኖሚ አቅሟ የቀጣናው አንቀሳቃሽ ሞተር የሆነችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ የቀጣናውን ሰላም የሚያጸና እንጂ የሚያናጋ አይደለም።
ሕጋዊ ስምምነቶችን፣ የጋራ ልማትንና የቀጣናዊ ትስስር መርሕን በመከተል ይህንን ታሪካዊ መብት ማስከበር ከ130 ሚሊየን ለሚሆን ሕዝብ ሕልም እውን የሚያደርግ ወሳኝ ርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለማግኘት የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና የዓለም ማሕበረሰብ ሊደግፈው የሚገባ የፍትሕ ጥያቄ ነው።
በሶስና አለማየሁ