አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የዝናብ ወቅት አልፎ ምድር ወደ አረንጓዴነቷ ስትመለስ፣ ወንዞች የሚረጋጉበትና ከክረምት ወደ አዲስ ወቅት የሚሸጋገርበት ጊዜ ይመጣል።
ከክረምት ወደ አዲስ ወቅት በሚደረገው በዚህ ሒደት የተፈጥሮ መታደስ ብቻ ሳይሆን የሰው ልብ ከቂምና በቀል ወደ ይቅርታ፣ ከመራራቅ ወደ መቀራረብና ከግጭት ወደ ሰላም ይሸጋገራል፡፡
ይህ ወቅት ለኦሮሞ ሕዝብ የምስጋና፣ የይቅርታ፣ የእርቅና የአብሮነት ልዩ ትርጉም ያለው ነው። ይህንን ትርጉም በሥነ ሥርዓትና በባህላዊ ክዋኔ የሚገልጸውም ኢሬቻ ነው።
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ የክረምት ወቅት በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ ሁሉን ነገር ለፈጠረው ዋቃ ምስጋና የሚያቀርብበት ባህላዊ በዓል ነው።
በዓሉ ለፈጣሪ ምስጋና ከማቅረብ ባለፈ፣ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ቁርኝት፣ የማኅበረሰብ እሴቶችንና የጋራ ሕይወትን የሚያሳይ ሥነ ሥርዓት ነው።
በዚህ ሥርዓት ውስጥ ኢሬቻ ምስጋናን ከማቅረብ ባለፈ ሰዎች የተራራቁ ግንኙነቶችን እንዲያድሱ፣ የተቀያየሙ ሰዎች እንዲታረቁና ማኅበረሰቡ በአንድነት አዲሱን ወቅት እንዲቀበል የሚያግዝ ማኅበራዊ መድረክ ሆኖ ይገለጻል።
በክረምት ወቅት በዝናብ፣ በወንዞች ሙላትና በሌሎች የተፈጥሮ ሁኔታዎች ምክንያት ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማዶች ተራርቀው ሊቆዩ ይችላሉ። የዝናብ ወቅት ሲያልፍ ግን ወንዞች ይረጋጋሉ፣ መንገዶች ይከፈታሉ፣ ተራርቀው የነበሩ ሰዎችም ይገናኛሉ።
በዚህ ተፈጥሯዊ ሒደት ውስጥ ኢሬቻ ልዩ ትርጉም ይይዛል። ከክረምት ወደ ብርሃን፣ ከመራራቅ ወደ መቀራረብ፣ ከቂም ወደ ይቅርታና ከግጭት ወደ ሰላም የሚደረግ ሽግግርን እንደሚያመለክት አባገዳዎች ይናገራሉ፡፡
የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት ከውኃ ጋር ያለው ቁርኝትም የዚህን ትርጉም ያጠናክራል። በኦሮሞ የባህል እሳቤ ውኃ የሕይወት፣ የንጽሕናና የተፈጥሮ ምንጭ ነው። ስለዚህ ኢሬቻ በውኃ ዳርቻ መከበሩ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥልቅ ትስስር ያሳያል።
የኢሬቻ ታዳሚዎች አረንጓዴ እርጥብ ሣርና አበባ ይዘው ወደ ሆራ፣ ማለትም በዓሉ ወደ ሚከበርበት የውኃ ዳርቻ ያቀናሉ። በዚያም በመሰባሰብና በሕብረት ለፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና ያቀርባሉ፤ ለመጪው ዘመንም ሰላምና በረከትን ይመኛሉ።
በዚህ ሥነ ሥርዓት የተፈጥሮ መልሶ መታደስ ከሰው ሕይወት መታደስ ጋር ተያይዞ ይታያል። አረንጓዴ ሣርና አበባ የአዲስ ወቅትና የተስፋ ምልክት ሲሆኑ÷ ውኃው ደግሞ የሕይወትና የንጽሕና ምንጭነቱን ያሳያል።
ኢሬቻ የምስጋና በዓል ብቻ አይደለም። የይቅርታና የመታረቅ እሴትንም ያጎላል። በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ሰዎች ያለፈውን ቂምና ቅሬታ በመተው አዲሱን ወቅት በሰላም እንዲቀበሉ ይበረታታሉ።
ኢሬቻ በኦሮሚያ ክልልና የኦሮሞ ሕዝብ በሚኖርባቸው ሌሎች አካባቢዎች በተለያዩ ሥፍራዎች ይከበራል። ከዋና ዋና የአከባበር ሥፍራዎቹ መካከል በቢሾፍቱ የሚገኘው ሆራ አርሰዲና በአዲስ አበባ የሚገኘው ሆራ ፊንፊኔ ይጠቀሳሉ።
በዓሉ ላይ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ቄሮዎችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ። ባህላዊ ልብሶች፣ ጭፈራዎች፣ የፈረሰኞች ትርኢትና ሌሎች ባህላዊ ክዋኔዎች የበዓሉን ድምቀት የሚያጎሉ ክዋኔዎች ናቸው፡፡
በአባ ገዳዎችና በሀደ ሲንቄዎች መሪነት የምስጋና ሥነ ሥርዓቱ ይከናወናል። የባህላዊ ዝማሬ፣ እልልታና ጭፈራ በአከባበሩ ውስጥ ጠቃሚ ሚና አላቸው።
ኢሬቻ የባህል ልብስ፣ ጭፈራ፣ ዝማሬና ሌሎች ክዋኔዎች የሚታዩበት በዓል ነው። በተለይ በዓሉ በትልልቅ የአከባበር ሥፍራዎች ሲከበር የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን የለበሱ ታዳሚዎች የበዓሉን ድምቀት ምልዑ ያደርጉታል።
ይህ የአከባበር መልክ የውበት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የባህል ልብሶች፣ የሥነ ሥርዓት ቅርጾች፣ ዝማሬዎችና ባህላዊ ዕውቀቶች ከአዛውንት ወደ ወጣት እንዲተላለፉ የሚያደርጉ የባህል መሸጋገሪያዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ኢሬቻ በርካታ ሰዎችን በአንድ ሥፍራ የሚያሰባስብ ትልቅ ባህላዊ ክንውን ሆኗል። የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በአንድ ሥፍራ ተገናኝተው ባህላቸውን ያሳያሉ፣ ይጠያየቃሉ፣ የጋራ እሴቶቻቸውንም ያጠናክራሉ።
በተለይ ሆረ አርሰዲና ሆረ ፊንፊኔ የመሳሰሉ የአከባበር ሥፍራዎች የሥነ ሥርዓቱ መከናወኛ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሰዎች የሚገናኙባቸው፣ የባህል እውቀት የሚለዋወጥባቸውና የጋራ ማንነት የሚገለጽባቸው ቦታዎች በመሆናቸው ህብረብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከርና ለማጽናት የጎላ ሚና አላቸው።
ኢሬቻ በዚህ መልኩ ያለፈውን ከዛሬ ጋር፣ ዛሬንም ከነገ ጋር የሚያገናኝ ሕያው ባህላዊ ቅርስ ሆኖ ይቀጥላል። የምስጋና ሥነ ሥርዓቱ፣ የይቅርታና የእርቅ እሴቱ፣ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ቁርኝትና የአብሮነት መልዕክቱ በየዓመቱ በአዲስ ትውልድ ይታደሳሉ።
ኢሬቻ የአንድ ቀን በዓል ብቻ ሳይሆን፣ ምስጋናን፣ ይቅርታን፣ እርቅን፣ ሰላምን፣ አብሮነትን፣ የተፈጥሮ ክብካቤንና የባህል ቅብብሎሽን በአንድ ላይ የሚያስተሳስር ትልቅ ባህላዊ ትሩፋት ነው።
የክረምት ወቅት አልፎ አዲስ ወቅት ሲጀምር፣ ኢሬቻም ያለፈውን በምስጋና ለመዝጋትና መጪውን በሰላም፣ በተስፋና በአብሮነት ለመቀበል የሚገልጽ ሕያው የባህል መገለጫ ሆኖ ይቆያል።
የዘንድሮው ኢሬቻ “ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ሃሳብ በሆረ ፊንፊኔ መስከረም 23 እንዲሁም በሆረ ሀርሰዴ መስከረም 24 ቀን 2019 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ይከበራል።
በመላኩ ገድፍ