የሀገር ውስጥ ዜና

የግብፅየዘመናት ሴራ እና የኢትዮጵያ የማይበገር የልማት ጉዞ

By emebet sisay

October 01, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበራትን ብቸኛ ተፅዕኖና የበላይነት ለማስጠበቅ ስትል ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭትና በጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ የመዝፈቅ ረጅም ታሪክ እንዳላት የውሃ ፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪዎች በስፋት የጻፉበት ጉዳይ ነው።

ከ1950ዎቹ እስከ 1990ዎቹ ባሉት አራት አሥርተ ዓመታት ካይሮ የኢትዮጵያን የውስጥ ደኅንነት ለማወክና ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ለማድረግ የሚያስችላትን ስትራቴጂያዊ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ስትፈጽም ቆይታለች። ለዚህ ደግሞ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን ትብብር ማግኘቷ ልፋቷን አቅሎላታል፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋማት መረጃዎች እንደሚያስረዱት፣ በፕሬዝዳንት ገማል አብደል ናስር እና አንዋር ሳዳት ዘመን ግብፅ በኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አማፂያንን እና ተገንጣይ ቡድኖችን በገንዘብ ድጋፍ በማጠናከር የኢትዮጵያን የውስጥ ግጭቶች ታራግብ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው።

በተጨማሪም በተለያዩ ጸረ-ኢትዮጵያ የትጥቅ እንቅስቃሴዎች ጀርባ ሁሉ እጇን በማስገባት ኢትዮጵያ ትኩረቷን ወደ ዓባይ ወንዝ ልማት እንዳታዞር ስታስተጓጉል ቆይታለች። ይህ አልበቃ ብሏት ግብፅ ለበርካታ ዓመታት የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ በወንዞቿ ላይ ለምታካሂዳቸው የልማት ፕሮጀክቶች ብድር እንዳይሰጡ ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እና ጉትጎታ ስታካሂድ ቆይታ ነበር፡፡

ከአረብ የጸደይ አብዮት በኋላም የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርን ተከተሎ፣ የካይሮ ስትራቴጂ ወደ ግልጽና ህቡዕ ሚዲያና ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ተቀየረ። ግብፅ ግድቡ “የውሃ ደኅንነቴን የሚጎዳ ነው” የሚል የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በዓረብ ሊግ በመንዛት፣ ግድቡን የፀጥታ ስጋት አድርጎ የማቅረብ (securitization) አካሄድ ተከተለች፡፡ ይህ መፍጨርጨሯ ፍሬ አልባ ቢሆንም አሁንም ከዚሁ ትርክት ፈቀቅ ለማለት ፍላጎት አላሳየችም፡፡

ይህ የቀደመ ታሪካዊ የግብፅ አካሄድ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ ቀጥሏል። በቅርቡ ግብፅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጁን እያሰገባ ላለው የሻዕቢያ መንግሥት ማንኛውንም ድጋፍ እንደምታደርግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻለች፡፡ ሻዕቢያ ከሕገወጡ የህወሓት ቡድንና ሌሎች ታጣቂዎች ጋር “ፅምዶ” ሲሉ የሰየሙትን ግንባር ፈጥረው ኢትዮጵያን የማበጣበጥና ከልማቷ የማደናቀፍ ተግባር ላይ ተሰማርቷል፡፡ ይህን ቡድን ከጀርባ ሆና የምትዘውረው እና ግፋ በለው የምትለው ካይሮ ናት፡፡

ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት በቀይ ባሕር ላይ ቁጥጥር የነበራት ሲሆን፣ በተገንጣይ ቡድኖች እና በውጭ ጠላቶች ደባ በ1980ዎቹ ወደብ እንድታጣ ተደርጋለች፡፡

የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን በብሔራዊ አጀንዳነት ያቀረበ ሲሆን፣ ከኃያላን ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ድጋፍ ማግኘት ተችሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ቁልፍ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

 

ይህን የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄ ግብፅ በጽኑ ስትቃወመው ይስተዋላል፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ መገኘት ለማረጋገጥ የምታደርገውን ማንኛውንም ጥረት እንደምትቃወም ገልጻለች፡፡

 

ግብፅ አንዲት ጠብታ ውሃ አስተዋፅኦ በማታደርግበት እና ኢትዮጵያ ከ85 በመቶ በላይ ለዓባይ ውሃ አስተዋፅኦ የምታደርግበት የዓባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ ወንዙን ማልማት የለባትም በማለት፣ በሌላ በኩል ሀገራችን በቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ የምታነሳውን ፍትሐዊ ጥያቄ ትቃወማለች፡፡

 

ይህ የግብፅ ድርብ መመዘኛ ያስገረማቸው የቀድሞው የአሜሪካ ጉምቱ ዲፕሎማት ቲቦር ናጊ “ግብፅ የአስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔ የመስጠት መብት ያላቸው የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት ብቻ ናቸው የምትል ከሆነ፣ የዓባይ ወንዝ አጠቃቀምን በተመለከተም ውሳኔ የመስጠት መብት ሊኖራቸው የሚገባው ለዓባይ ውኃ የሚያዋጡ ሀገራት ብቻ ይሆናል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

ሆኖም እነዚህ ተደራራቢ የውስጥና የውጭ ተፅዕኖዎች የኢትዮጵያን የልማት ጉዞ ሊያስቆሙ አልቻሉም። የጂኦፖለቲካዊ ጫናዎችና የውስጥ ፈተናዎች ሳይበግሯት ታላቁን ሕዳሴ ግድብ በራሷ አቅም ገንብታ ማጠናቀቋ የዚህ ጽናት ትልቅ ማረጋገጫ ነው።

ኢትዮጵያ የግብፅን የሐሰት ስጋትና ስሞታ ውድቅ ለማድረግ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመሠረተ የውሃ አሞላልና አጠቃቀም በመከተል፣ የታችኞቹን ሀገራት ጉዳት በማይዳርግ መልኩ ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ ለቀጣናው የጋራ ልማትና ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀም ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች።

በቴዎድሮስ ሳህለ