የሀገር ውስጥ ዜና

የካይሮ ቅዠት እና ተላላኪዋ አስመራ

By Melaku Gedif

October 02, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የጂኦ ፖለቲካዊ መድረክ ላይ የሚታዩት ተለዋዋጭ ክስተቶች ፍንትው አድርገው የሚያሳዩት አንድ ሀቅ አለ፤ ይህም የካይሮ እና የአስመራ ስልታዊ ፍርሃት ምንጩ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና የመሆኑ ነገር ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ፣ የሕዝብ ቁጥርና ስትራቴጂካዊ የበላይነት ተጠቅማ የቀጣናውን የኢኮኖሚ ትስስር እውን ለማድረግና አህጉራዊ ትንሳኤን ለመምራት በምትተጋበት እያንዳንዱ ሰከንድ፣ በካይሮና በአስመራ ቤተ መንግሥቶች ውስጥ የሚሰማው የቅዠት ዋይታ የትዝብት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

ኢትዮጵያን በታሪካዊ ስህተትና ሴራ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ የተደረገበት የጨለማ ምዕራፍ ቢያበቃም፣ ዛሬ ያንን ስህተት ቀልብሶ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብርሃን መፈንጠቅ፣ ሁለቱን የኮንትሮባንድ ሰላም አራማጆች ክፉኛ አስደንብሯቸዋል።

ካይሮ በቀጣናው ልማትና በጋራ ተጠቃሚነት ስም በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ውስጥ መሳተፍን እንደ ታሪካዊ ሽንፈት ትቆጥራለች።

ምኞትና ስትራቴጂዋ ጎረቤቶቿ በግጭት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው ከድህነት እንዳይወጡ በመስራት የናይል ውኃን ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ለብቻዋ የመጠቀም ዘመኑን የማይመስል ቅዠቷን መኖር ነው።

ለዚህ እኩይ ህልሟ ስኬት ደግሞ የልማት አማራጮችን ከመደገፍ ይልቅ፣ በቀጣናው ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ ሌት ተቀን ትቋምጣለች። ይሁንና ይህንን እሳቷን ለማንደድ ራሷ በቀጥታ ወደ ሜዳ ከመግባት ይልቅ፣ በፈለገችው መንገድ የምትጋልባቸው ባዕዳንና የውስጥ ባንዳ ፈረሶቿን በጥቅም መያዝን ትመርጣለች።

ይህ ደግሞ ካይሮንና አስመራን ባልተቀደሰ ጋብቻ አቆራኝቷቸዋል። ካይሮ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የውስጥ የኢኮኖሚ ውጥረት፣ የገንዘብ ግሽበትና የማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። ይህንን የውስጥ ህዝባዊ ቁጣና ውድቀት ለማስታገስና ትኩረትን ለማስቀየር ደግሞ፣ ወደ ውጭ የሚተኮስ የጠብ አጫሪነት አጀንዳ ያስፈልጋታል።

ለዚህ ፍላጎቷ ታማኝ ፈረስ ሆኖ የሚያገለግለው የአስመራ ገዥ ቡድን የጥይት ቀለብ እና የጦር መሣሪያ እየሰፈረች ውጥረቷን ለማስታገስ ትሞክራለች። ይህ ለአስመራ የሚደረገው የጦር መሣሪያ ድጎማ ግን የልማት ሳይሆን፣ የቀጣናውን ህዝብ በደም እሳት የመለብለብ የቁማር ጨዋታ ነው።

በዚህ የካይሮ የሴራ ፈረስ ውድድር ላይ ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ ይዞ የሚገኘው የአስመራው ገዥ ቡድን ነው። የኤርትራ አስተዳደር ከፍጥረቱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ አልፎ ተርፎም ታሪክ አከተመለት ተብሎ እስከሚሰናበትበት የመጨረሻው ቀን ድረስ፣ ከቅጥረኝነትና ከተላላኪነት ቀንበር ሊወጣ የማይችል የታሪክ እጣ ፈንታ ተጭኖበታል።

ጠንካራ፣ ሰላማዊና የበለጸገች ኢትዮጵያ መኖር ለራሱ የፖለቲካ ሕልውና እንደ ትልቅ ስጋት የሚቆጥረው ይህ ስብስብ፣ የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ከሚሰሩ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ማበርን እንደ ትልቅ የፖለቲካ ጥበብ ይቆጥረዋል። አስመራ በበኩሏ ከቀይ ባህር ማዶ የሚመጣላትን በጥቅም የታጀበ የጦር መሣሪያ ኮንትሮባንድ እንደ ትልቅ ስኬት ትቆጥረዋለች።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀይድሮ-ፖለቲካ እውነታ የኋሊት እንደማይመለስ ሴረኞቹ ሊረዱት አልቻሉም። በፈረንጆቹ 2013 በሞሃመድ ሙርሲ አስተዳደር የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሳይቀር የታቀዱት አፍራሽ የጥፋት አማራጮች እንደከሸፉት ሁሉ፣ አሁን በኤል-ሲሲ የሚመራው የጂኦ ፖለቲካዊ ከበባ እና የቀይ ባሕር ወታደራዊ ስምምነትም የታሪክ መድገሚያ ከመሆን አይዘልም።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተርባይኖች ማመንጨት የጀመሩት ብርሃን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ልዕልና የሚያበስር ብቻ ሳይሆን፣ የቀጣናውን የጨለማ ሴራ የሚያጋልጥ የእውነት ጸዳል ነው።

በካይሮ የጥይት ቀለብ የሚደንሱ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ሲነካ የሚመጣውን የተባበረ ኃይልና ዲፕሎማሲያዊ መገፋት መቋቋም እንደማይችሉ የትናንቱ የዲፕሎማቶች መባረር ህያው ማረጋገጫ ነው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ዲፕሎማቶች የዲፕሎማሲያዊ ከበሬታ መብትን ሽፋን በማድረግ የሀገርን የሰላም ፅኑ አቋም ሲፈታተኑት በመስተዋሉ፣ ኢትዮጵያ በአስመራ የሚገኘው ኤምባሲዋ እንዲዘጋ መወሰኗ እና የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሀገር ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ፣ ለሉዓላዊነቷና ለክብሯ የምትሰጠውን ዋጋ በተግባር ያሳየ ጥልቅና ወቅታዊ ርምጃ ነው።

የካይሮ የገንዘብ አለንጋ እና የአስመራ የቅጥረኝነት ስላቅ የቱንም ያህል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ቢረጩም፣ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለአፍታም ቢሆን ሊገቱት አይችሉም። የታሪክ እውነታ እንደሚያስተምረን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደህንነት የሚረጋገጠው የላይኛውን ተፋሰስ ጎረቤትን በማናጋት ሳይሆን በፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ብቻ ነው።

ሴረኞች በራሳቸው እኩይ ምኞት ወጥመድ ውስጥ መውደቃቸው የማይቀር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን የቀጣናውን ሰላም የማስከበርና የሕዝቦቿን ታላቅነት የማረጋገጥ ታሪካዊ ተጋድሎዋን በፅናትና በልዕልና ትቀጥላለች።

ኢትዮጵያ በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ የሚቃጡትን ሁለንተናዊ ትንኮሳዎች የመመከት፣ ሉዓላዊነቷን የማስከበር እና የባሕር በር ባለቤትነትን የማስጠበቅ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት አላት። ይህንን ሕጋዊ መብቷን በማንኛውም ዋጋና በሁሉም ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተግባር ትጠቀምበታለች።

በኃይለኢየሱስ መኮንን