አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት ዝቅትኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫናን ለመቀነስና የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡
እነዚህ ስትራቴጂያዊ ተግባራት በዋናነት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የከተሞች ማህበራዊ ሴፍቲኔት መርሐ ግብሮችና የገጠር የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮጀክቶችን በማቀናጀት ዜጎችን ከዕለት እርዳታ ጥገኝነት ራስን ወደ መቻል ለማሸጋገር ያለሙ ናቸው።
መንግሥት የፋይናንስ አገልግሎቶች (ብድርና ቁጠባ) ወደ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴት ስራ ፈጣሪዎችና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲደርሱ በማድረግ የገቢ ምንጭ መፍጠሪያ መንገዶችን እያሰፋ ይገኛል፡፡
ለአብነትም ለተቀጣሪዎች የሚሠራው የደመወዝ ገቢ ግብር ስሌትና የእርከን ደረጃዎች ላይ ትልቅ ማሻሻያ ተደርጓል።
በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የኑሮ ጫናን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የተነደፉ ውጤታማ ተሞክሮዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡
በገጠር አካባቢዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው፡፡
አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችና የተሻሻሉ የዘር ዝርያዎችን በቅናሽ ዋጋ የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል።
በተጨማሪም በሌማት ትሩፋት መርሐግብር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶችና ወጣቶች በዶሮ እርባታና በወተት ላሞች ማህበራት ተደራጅተው የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ተደርጓል።
በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት አርሶ አደሮች ለችግር እንዳይጋለጡ በበጋ መስኖ ስንዴና መሰል ፕሮጀክቶች አርሶ አደሩ ራሱን እንዲችል የሚያስችሉ ሥራዎች ተተግብረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የኑሮ ውድነትን ጫናን ለማቃለልና የአርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በህብረት ስራ ማህበራት ምርታቸውን በቀጥታ ወደ ሸማቾች ማዕከል እንዲያቀርቡ የተደረገበት የትስስር ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል።
በተጨማሪም በየዓመቱ ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ነፃ ደብተር፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችና የተማሪዎች የደንብ ልብስ በነፃ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴና ዱቄት ያሉ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች በከተማዋ ባሉ የሸማቾች ማህበራትና የእሁድ ገበያ ማዕከላት አማካኝነት ከመደበኛ የገበያ ዋጋ በታች ለህብረተሰቡ ይቀርባሉ።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በትዕግስት ግዛቸው