አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች የተገኙ የአጀንዳ ምክረ-ሀሳቦችን በአግባቡ በማደራጅትና በኮሚሽኑ ምክር ቤት በማፅደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረክቧል።
ኮሚሽኑ በ284 ገፆች የተቀነበበ፣81 እጅግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የቀረቡ ምክረሀሳቦችንና 400 ዝርዝር ምክረ-ሀሳቦችን የያዘውን ሰነድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አስረክቧል፡፡
በተጨማሪም ኮሚሽኑ በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና በፌደራል ተቋማት ደረጃ ባካሄዳቸው ምክክሮች የሰበሰባቸውንና በክልል መንግስታት፣ በከተማ አስተዳደሮች እና በፌደራል መንግስት መፈታት ያለባቸውን አጀንዳዎች ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ለፌደራሉ መንግስት በክብር አስረክቧል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን ዓርዓያ ባቀረቡት ሪፓርት ÷ይህ የሀገራዊ ምክክር ሂደት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ታሪካዊ ሂደት መሆኑን አንስተዋል።
ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን አበርክቶ ለነበራቸው አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው÷ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ኮሚሽኑ ያስረከባቸውን አጀንዳዎች ተገቢውን እቅድ አውጥተው በአግባቡ እንዲሰሩበት አሳስበዋል።
ለምክር ቤቱ የቀረበው ምክረ-ሀሳብም በአስፈፃሚው አካል በትኩረት እንዲተገበር ተገቢው ክትትል ይደረጋል ያሉት አፈ ጉባኤው÷ኮሚሽኑን በመምራት ለዚህ ስኬት ላበቁት ኮሚሽነሮችና ባለሙያዎች እውቅና ሰጥተዋል።