አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ዜጋ አይኖራትም አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
የአዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታና የ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን የምክር ቤቱ መመስረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
ምክር ቤቱ በስብሰባው ላይ ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሰይሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በድምጻቸው ቅቡል መንግሥት ለማጽናት ለታመኑ ከ54 ሚሊየን በላይ መራጮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ የዴሞክራሲ ባህልም የሚፈተነው በምርጫ ወቅት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሕዝቡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሕልውናውን ለማጽናት መምረጡን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ ሒደቱ የዴሞክራሲያዊ ባህላችን መሰረቱ እየጠነከረ መምጣቱን በግልጽ አሳጥቷል ብለዋል፡፡
ማንኛውም ምርጫ አሸናፊና ተሸናፊ ፓርቲ ሊኖረው ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ ግን አሸናፊ እንጂ ተሸናፊ ዜጋ እንደማይኖራት አረጋግጠዋል፡፡
እንደ ሀገር የሚጠብቀንን ፈተና መሻገር የምንችለው እንደ ወንድማማች ተያይዘን እኩል መራመድ ስንችል ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በመላኩ ገድፍ