የሀገር ውስጥ ዜና

የምክር ቤት አባላት የተጣለባችሁ ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት በእጅጉ ከፍ ያለ ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ

By sosina alemayehu

October 06, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት የተጣለባችሁ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ኃላፊነት በእጅጉ ከፍ ያለ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 7ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት የጋራ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የሁለቱ ምክር ቤት ተመራጭ አባላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ስብሰባውን በይፋ ያስጀመሩት ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋሚ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሰየማቸው እንኳን ደስ ያለዎት ብለዋል፡፡

ተመራጮች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብን ይሁንታ አግኝተው የምክር ቤቶቹ አባል በመሆናቸውም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ይህ ታላቅ ምክር ቤት የመንግሥት ስልጣን መሰረቱ እና ምንጩ የሰፊው ሕዝብ ይሁንታ እና ድምጽ እንደሆነ የሚረጋገጥበት ሕያው ማህተምና ምስክር መሆኑን አውስተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች የምታከናውኗቸው ሥራዎች እና የምትደነግጓቸው ሕጎች ለዘመዊዋ ኢትዮጵያ የሥልጣን መንገድ በሕዝብ የይሁንታ ድምጽና ቅቡልነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የተጣለበችሁ ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት በእጅጉ ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡

ስለዚህ የመረጣችሁ ሕዝብ ከአመኔታ ጋር ታላቅ አደራ የሰጣችሁ በመሆኑ ይህንን ኃላፊነተ በታላቅ አስተዋይነት፣ ጥበብ፣ ብልሃት እና ታታሪነት እንደምትወጡ የኢትዮጰያ ሕዝብ ያምናል ነው ያሉት፡፡

ሁለንተናዊ ዝግጅታችሁም ይህንን አደራ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚያሸጋገር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በመላኩ ገድፍ