የሀገር ውስጥ ዜና

የምክር ቤት አባላት ሰላም ማጽናትና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል – ፕሬዚዳንት ታዬ

By sosina alemayehu

October 06, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የምክር ቤት አባላት የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ማጽናት እንዲሁም ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።

የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት የጋራ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የሁለቱ ም/ ቤቶች ተመራጭ አባላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ የምክር ቤት አባላት ሁለንተናዊ ዝግጅት የመረጣቸው ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ የሚመጥን ብቻ ሳይሆን ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ስለሆነም የምክር ቤት አባላት ቀዳሚ ትኩረት መልካም አስተዳደርን የሚያዘምን፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ ይበልጥ ከፍ የሚያደርግና ምርታማነትን የሚያሳድግ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የኑሮ ውድነትን የሚገራ፣ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በስፋት የሚዘረጋ እና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያጸና መሆን አለበት ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተወሰዱ ርምጃዎች ለቀጣይ አፈጻጸም ብርቱ መሠረቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ የግብርና ሥርዓት ይሻሻል ዘንድ በሥራ ላይ የዋሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂና የመስኖ መሠረተ ልማት፣ የማዕድን ሥራ፣ የቱሪዝም መዳረሻ መጠናከርና የዲጂታል መሠረተ ልማት ማደግን ጠቅሰዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የመፈጸም አቅምና ልምድን በማዳበር በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የሚፈጸሙ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ይበልጥ ውጤታማ እየሆኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሀገራችንን የደን ሽፋን ጉልህ በሆነ መንገድ መጨመሩንና የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ አስደናቂ ለውጥ ማምጣቱን ነው ያወሱት።

እነዚህና መሰል ሥራዎች በበርካታ አካላት አድናቆት ያተረፉና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ አብነት የሚነገርላቸው ስኬቶች መሆናቸውን አውስተዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በመላኩ ገድፍ