የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት ይሰራል – ከንቲባ አብዱላሂ አደን

By tigist gizachew

October 06, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል አሉ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደን።

የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የውሃ፣ የመንገድ እና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል።

ከንቲባ አብዱላሂ አደን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አስተዳደሩ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቷል።

ዘላቂ ሰላምና ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ከማጠናቀቅ ጎን ለጎን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ ብለዋል።

ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው በጀት እና ጊዜ ለማጠናቀቅም ነዋሪዎችንና ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት እንደሚሰራ አንስተዋል።

በተለይም በገጠር እና በከተማ የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

አመራሮቹ በጉብኝታቸው የቢሮ የሥራ እንቅስቃሴዎችን፣ የድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥ እና የሕዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አፈታት ሁኔታን መመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡