አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት አሃድ በማስረከብ ወደ ተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቅርቧል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ በመግለጫቸው ÷ ኮሚሽኑ ከሕዳር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ አድርጓል።
መንግሥት በትግራይ ክልል ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑንም አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሕገ ወጡ ሕወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው ስምምነት የፈረመውን ትጥቅ የማስፈታት ስምምነት በማፍረስ ወደ ተሃድሶ ማዕከል ለመግባት ፈቃደኛ የነበሩ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና እንዳይወስዱ ሲያደናቅፍ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ወጣቶችን አስገድዶ በማፈስ ለሌላ ጦርነት ሲያዘጋጅ እንደነበር ነው የገለጹት።
በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ መንግሥት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የመልሶ ማቋቋም መርሐ ግብሩ እንዳይቋረጥ ሰፊ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት መንግሥት አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህም በትግራይ ክልል የሰላም መንገድን መርጠው ወደ ፌደራል መንግሥት የሚመጡ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ስለሆነም በትግራይ ክልል የቀደሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት አሃድ እያስረከቡ ወደ የተሃድሶ ማዕከል እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም መንግሥት በርካታ ሃብት መድቦ ዜጎችን ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡