የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ታጣቂዎች በመቐለ አካባቢ የተዘጋጀው ተሃድሶ ማዕከል

By tigist gizachew

October 06, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለተወሰኑ ግለሰቦችና ጽንፈኞች ተብሎ የትግራይ ወጣት በጭፍን አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል የለበትም አሉ የብሔራዊ ተሃድሶ ምክትል ኮሚሽነር ብ/ጄ ደርቤ መኩሪያው፡፡

ብ/ጄኔራል ደርቤ በሰጡት መግለጫ ÷ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለሚመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ሕይወት ለማስገባት መንግሥት አሁንም በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሕዳር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

የትግራይ ወጣት ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለስ መንግሥትና የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ወጣቶችና ታጣቂዎች መንግሥት ለመቀበል ዝግጁ በመሆኑን አውቀው ሳይረፍድ የቀረበውን የሠላም አማራጭ እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል፡፡

ታጣቂዎቹ በቡድንም ሆነ በተናጠል መቐለ አካባቢ በተዘጋጀው የተሃድሶ ማዕከል ወይም በየአካባቢው ለሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት ሪፖርት ማድረግ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡

አሁንም በመከላከያ ሠራዊት ዩኒት እጅ ከእነ ትጥቁ የገቡ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውን ነው ብ/ጄ ደርቤ ያመላከቱት፡፡

ወጣቱ ከጦርነትና እሳት በመውጣት ማንኛውንም የጦር መሳሪያ ቁሳቁስ ለመከላከያ ሠራዊት በማስረከብና ሪፖርት በማድረግ ወደ ተሃድሶ ኮሚሽን እንዲቀላቀልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡