የሀገር ውስጥ ዜና

በምርጫ ያበበው ተሳትፎ በልማት ሲደገም

By sosina alemayehu

October 07, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀላሉ አይገነባም፣ የጋራ ርዕይ መያዝን፣ በትጋት መስራትን፣ በትብብር መንፈስ አብሮ መቆምን፣ ዓላማን ከግብ ለማድረስ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ያሳየው ቁርጠኝነት ለዓላማ የመፅናት መልክ ነው፤ ለዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት፣ ለመብት መከበርም የተከፈለ ውድ ዋጋ ነው፡፡

ዓለም በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፈተናዎች ስትናጥ፣ ኢትዮጵያም ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች ወደ እድል ቀይራ እየተጓዘች ያለችው በዜጎች ትዕግስትና ፅናት እንዲሁም በአመራር ቁርጠኝነት ነው፡፡

ሀገር “እኔ ብቻ” በሚልና ልዩነትን ብቻ ማዕከል ባደረገ አካሄድ አትገነባም፣ አትጸናምም፡፡ ይልቁን ይህንን ልዩነትን በማክበር፣ አለመግባባትን በውይይት በመፍታት ሰላሟን ታፀናለች፡፡

ሰላሟ በተከበረ ሀገር ላይ የሚኖሩ ዜጎች ከውጭ የሚሰነዘር ሀገርን የማተራመስ አጀንዳ ለማራመድ ለሚሹ ጠላቶች ሁሉ በሮችን ይዘጋል።

ሀገር የጸና ሰላም ሲኖራት፣ ዜጎች ትኩረታቸው ሁሉ ወደ ልማት ያዞራሉ፡፡ ዛሬም ህዝቡ ሀገሪቱን ወደ ልማትና ዕድገት በሚመሩ ተግባራት ላይ በቁርጠኝነት እየተሳተፈና እየገነባ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለመገንባት የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ በመታገስ አልፋ ለፍሬ ስታበቃ የህዝብና የመንግሥት የተናበበና የተቀናጀ ጥረት የጎላ አስተዋጽኦ ነበረው።

የግድቡን ፕሮጀክት ለማደናቀፍ የተካሄደው የሴራ ዘመቻ ሳይገድባት፣ ህዝቦቿ በደምና በላባቸው ባሳዩት ትጋትና በከፈሉት ውድ ዋጋ ዓላማቸውን ከግብ አድርሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላም የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ብዛት ያላቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየገነባች ትገኛለች፡፡ ታድያ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ውጤታማነት የመደመር መንግሥት ጥረቶች ላይ የዜጎች ትጋትና ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

#ኢትዮጵያ #የመደመር_መንግሥት

በቤተልሔም ግርማ