አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ጊዜያት የተደረጉ ሰፊ ውይይቶችን መነሻ በማድረግ በቀጣይ አምስት ዓመታት ከመደመር ግራንድ ስትራቴጂ የተቀዱ ተግባራት በየደረጃው ተፈጻሚ ይሆናሉ አሉ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የካቢኔ ዕጩዎችን አቅርበዋል ፤ምክር ቤቱም የቀረበውን የእጩዎች ሹመት አጽድቋል።
በዚህም ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በድጋሚ የገቢዎች ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽና ጋር ባደረጉት ቆይታም ፥ ህዝብ መንግስትን አምኖ በድጋሚ የመረጠበትን ምክንያት በመገንዘብ፣ የህዝብን ፍላጎትና ተጠቃሚነት ሊመልሱ የሚችሉ ዝግጁነቶች ተደርገዋል ብለዋል።
ሀገራዊ አንድነትን፣ ሰላምን እና ጠንካራ ኢኮኖሚን በዘላቂነት ለመገንባት ከመንግስት ባለፈ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና የግል ሴክተሩ በየደረጃው ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አሁን ኃላፊነትን የተረከበው ካቢኔ ሀገራችንን ሰላማዊና አይበገሬ ኢኮኖሚ እንዲኖራት በማድረግ ሂደት ውስጥ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
ሚኒስትሯ በቀጣይ አምስት ዓመታት ከመደመር ግራንድ ስትራቴጂ የተቀዱ ተግባራት በየደረጃው ተፈጻሚ ይሆናሉ ብለው ለዚህም ስኬት አግባብነት ያለው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን አረጋግጠዋል።
#የመደመር_መንግሥት
በሶስና አለማየሁ