የሀገር ውስጥ ዜና

የጾታ ስብጥር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ እድገት

By sosina alemayehu

October 08, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የብዙ ዘመናት የመንግሥታት ታሪክ ያላት እና ብዙ መሪዎችን ያስተናገደች ሀገር ብትሆንም አብዛኛው ታሪኳ እና የስልጣን ተጋሪዎችዋ ወንዶች እንደነበሩ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡

በታሪክ ማህደር ስሟ ሰፍሮ የምትገኘው የአክሱም ንግስት ንግስተ ሳባን ጨምሮ ጥቂት የፖለቲካ ዘርፉ ላይ የነበሩ ከጣት ቁጥርም ያነሱ ሴቶች ቢኖሯትም አብዛኛው ፖለቲካዋ እና ሀገራዊ ጉዳዮቿን በወንዶች ጫንቃ ላይ ጥላ የኖረች ሀገር ናት፡፡

ታዲያ ይህ የወንዶች ብቻ ተሳትፎ የበዛበት ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እያደገ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ››፣ ‹‹ሴት ወደ ማጀት ወንድ ወደ ችሎት›› የሚሉት አጉል ስንኞች ማክተሚያቸው ደርሷል።

ሴቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በበቂ ተወክለዋል፣ በበቂ ተሳትፈዋል ፣በበቂ የሚገባቸው ቦታ ላይ ደርሰዋል፣ ማለት ባይቻልም ግን የሚታዩ ለውጦችን መካድ ግን አይቻልም፡፡

በአዲሱ የመደመር መንግሥት ይህ ጉዳይ በቃል ሳይሆን በተግባር እየታየ ነው፡፡

እኩልነት በቃል ሳይሆን በተግባር የሚገለፅ ነው፤ ስለ እኩልነት ሁሉ ይናገራል ግን ሁሉም እኩል አይተገብረውም፡፡

በተግባሩ የሚገለፀው የመደመር መንግሥት በዛሬው እለት 40 ከመቶ ሚኒስትሮቹን ሴቶች አድርጎ ሾሟል፡፡

ከ22ቱ ሚኒስትሮቹ ውስጥ 9 ሴት ሚኒስትሮችን ሾሟል፡፡

ይህም አካታችነትን መሰረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን ለቦታው ያለ ብቃትና ችሎታን ባማከለ መልኩ የተከወነ ነው፡፡

በቀደሙት ጊዜያት ኢትዮጵያ ላይ የሴቶች እኩልነት ይረጋገጣል ሲባል ቢቆይም በተግባር የሚታይ አልነበረም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በንግግራቸው ፡- ከ22 ሚኒስትሮች 9 ሴት ሚኒስትር ያደረገ አንድ ሀገር መጥራት አይቻልም፡፡ አደግኩ፣ ሰለጠንኩ በለፀግኩ የሚል፣ ስለሴቶች መብት ከኛ በላይ የሚያወራም ቢሆን ሁለት ሶስት ሰው ቢገኝ ነው ፡፡ በዚህ ረገድም ጥሩ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በዚህም ሴትና መስራት የምትችል በሚል መስፈርትን የተከተለ መሆኑ፣ ለኮታ መሟላት ብቻ ሳይሆን ሴቶች ያላቸውን አቅም ለማሳየት እና ለመጠቀም የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ በፆታ ስብጥር ጉዳዮች ላይ እድገት እያሳየ ነው ማለት ሲቻል፤ወደ ፊት ከዚህ የበለጠ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

#የመደመር_መንግሥት

በእመቤት ሲሳይ