የሀገር ውስጥ ዜና

አዲሱ ካቢኔ መደመር በተግባር – ጥንካሬን ማስቀጠል፣ አዲስ አቅም መጨመር

By sosina alemayehu

October 08, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ የተካሄደው የመደመር መንግሥት ሚኒስትሮች ሹመት በርካታ መልካም ተሞክሮዎችን ያስቀጠለ፣ አዳዲስ አሰራሮችን ያስተዋወቀ እና መጪውን ጊዜ ያመላከተ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዕጩዎችን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፣ የመመዘኛ መስፈርቱ ከዕጩዎቹ የትምህርት ዝግጅት እና የመፈጸም አቅም በማስከተል ፆታን፣ እምነትንና ብሔርን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

በዛሬው የሚኒስትሮች ሹመት ታዲያ ባለፉት አምስት ዓመታት የታዩ መልካም ተሞክሮዎች ተጠናክረው የቀጠሉበት እንዲሁም አዳዲስ ልምምዶች የታዩበት ሆኗል፡፡

ለአብነትም ከሐረሪ ክልል ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚኒስቴር ደረጃ በኃላፊነት የተሾመ ሲሆን፣ ከትግራይ ክልል ከለውጡ ወዲህ አንድ ብቻ የነበረው የካቢኔ አባል ብዛት በአሁኑ ወቅት ከክልሉ በጾታ እና በሃይማኖት ስብጥር ሁለት የካቢኔ አባላት እንዲሾሙ በማድረግ አካታችነትን እና ያለፈን ልምድ የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል፡፡

የመደመር መንግሥት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ በመሾም አዲስ የዴሞክራሲ ባህል ልምምድ በሀገራችን እውን ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ዛሬም በአዲሱ የመደመር መንግሥት ካቢኔ ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲካተቱ መደረጉ፤ ይህን አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ባህል የሚያዳብር እርምጃ ነው፡፡

ሌላው በዛሬው የመደመር መንግሥት አዲስ ካቢኔ ሹመት የተስተዋለ ጉዳይ ቢኖር ግማሽ ያህሉ የካቢኔ አባላት በሌሎች የሥራ ኃላፊነታቸው ባሳዩት አፈጻጸም፣ ልምድና የትምህርት ዝግጅት በሚኒስትርነት ለመሾም በቅተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የጾታ ስብጥርን በተመለከተ በአዲሱ የሚኒስትሮች ሹመት ሴቶች 40 በመቶ የሚሆነውን የካቢኔነት ሥልጣን አግኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የካቢኔው ሹመት ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸው፣ የካቢኔ አባላት ከወትሮ በተለየ መንገድ ባለዕዳና ከፍተኛ አደራ የተጣለባቸው መሆናቸውንና ዛሬ መሾም ሸክም መሆኑን እንዲገነዘቡ ማሳሰብ እፈልጋለሁ ብለዋል።

ሹመት ብዙ ምቾት፣ ብዙ እንቅልፍና ብዙ ድሎት ያለው ጉዳይ ሳይሆን ብዙ ኃላፊነትና ድካም ያለው ጉዳይ መሆኑን እያንዳንዱ ዕጩ የካቢኔ አባል ከወዲሁ እንዲገነዘብ እና ሥራውን በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲያከናውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የዛሬው የሚኒስትሮች ሹመትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ፣ የመጪውን ጊዜ የሕዝብ አገልጋይነት እና የሥልጣን አተያይ የሚቀይር አዲስ ምዕራፍ የሚያበስር ነው።

በቴዎድሮስ ሳህለ