አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) 19ኛው ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን በመጪው ሰኞ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በድምቀት ይከበራል፡፡
ቀኑ “ሠንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ሁነቱ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ዳር ድንበርና ክብር ለማስጠበቅ ደምና ላባቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያስከበሩት ሰንደቅ ዓላማ በጋራ የሚከበርበት ነው፡፡
በመሆኑም የዘንድሮው የሠንደቅ ዓላማ ቀን በምክር ቤቱ አስተባባሪነት በመላ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሀገራዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
በዕለቱ ፕሬዚዳንቱ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ማርሽ ባንድና ክብር ዘብ ታጅበው ሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ሥነ ሥርዓት ያከናውናሉ፡፡
ይህ በዓል በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በተመሳሳይ ሰዓት እንደሚከበር የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡