የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ ምዕራፍ በአዲሱ ሹመት

By tigist gizachew

October 09, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲሱ የመንግሥት ምስረታ ሀገሪቱ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምህዳሯ ውስጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገርበትና መጪውን የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን የምታውጅበት ታሪካዊ ክስተት ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ በቀደሙት ዓመታት ካደረጋቸው የመብት፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ትግሎች ብዙ ልምድ ቀስሟል።

የአመለካከት አድማሱ ሰፍቷል፣ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ስፋትና ጥልቀት ጨምሯል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአንድ በኩል ነጻነቱንና ሰብዓዊ መብቱን ለማስከበር መራራ ትግል እያካሄደ በሌላ በኩል ደግሞ “ምን ዓይነት ዴሞክራሲ” ነው የሚያስፈልገኝ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

በማንኛውም ሀገር ታሪክ ውስጥ የአዲስ መንግሥት ምስረታ ወቅት አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት፣ ያለፉ ስህተቶችን በማረም አዳዲስ ስኬቶችን ለማስመዝገብ የሚታቀድበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየታየ ያለው የመንግሥት ምስረታ ሂደትም በሕዝቡ ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ተስፋና ጉጉትን ፈጥሯል። ሕዝቡ አዲሱ መንግሥት ሀገርን ካለችበት ዘርፈ-ብዙ ፈተናዎች አሻግሮ፣ ፍትሃዊነትን በተግባር የሚያረጋግጥ እንዲሆን በጽኑ ይጠብቃል።

አዲሱ የመንግሥት ምስረታ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ድምፅና የብዝሃነት ውበት በተግባር የሚገለጽበት፤ በእኩልነትና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ እንዲገነባ መንገድ ይከፍታል።

ይህ አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ምስረታ የሕዝብን ማኅበራዊ ውልና አመኔታ ይዞ የሚመጣ በመሆኑ፣ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

መንግሥቱ የሀገሪቱን ሰላም የማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥና የዜጎችን መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች የመመለስ ትልቅ አገራዊ አደራ ያለበት በመሆኑ የአሁኑ የመንግሥት ምስረታ ከተለመደው የአግላይነት ፖለቲካ ወጥቶ የብዝሃነት ውበትን በተግባር የሚያሳይ፣ ሁሉንም ዜጋ ያካተተ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት አልሟል፡፡

አዲሱ አስተዳደር የተጀመሩትን የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታዎችንና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የማሻሻል ተግባራትን አጠናክሮ የመቀጠል ሚና ይኖርበታል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ ውስብስብ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፈተናዎችን በጽናት በመሻገር፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነትና አብሮነት በማጠናከር ወደ ተሻለ የልማትና የብልጽግና ምዕራፍ ትሸጋገራለች።

የመንግሥት ምስረታው የመዋቅር ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን፤ በመንግሥት እና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት በአዲስ መርሆዎች ላይ የመገንባት ማህበራዊ ውል ያደርጋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያን ከተደቀኑባት ዘርፈ-ብዙ ፈተናዎች ማሻገር የሚችለው፣ ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ እና የሁሉንም ዜጎች እኩል ተጠቃሚነት በተግባር ማሳየት ሲችል ብቻ ነው።

በአጠቃላይ የሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ ለመንግሥት ትልቅ ጉልበትም አደራም ነው። አዲሱ መንግሥት ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም የሕዝቡን ተስፋ ወደ ተግባር በመለወጥ ፍትሕ የሰፈነባት፣ የሁሉም ዜጎች መብት የተከበረባትና በጋራ የምትበለጽግ ጠንካራ ሀገር መመስረት ይቻላል፡፡

#የመደመር_መንግሥት

በትዕግስት ግዛቸው