የሀገር ውስጥ ዜና

የእስረኞች በይቅርታና ክስ መቋረጥ መፈታት የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ለማጠናከር አዎንታዊ ርምጃ ነው – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን

By Yonas Getnet

October 09, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፈው ዓመት ከ729 በላይ እስረኞች በይቅርታና ክስ መቋረጥ መፈታታቸው የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ ለማጠናከር አዎንታዊ ርምጃ ነው አለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም ባሉ ጊዜያት በኮሚሽኑ ክትትልና ምርመራ ላይ ተመስርተው የተገኙ ውጤቶችን ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በሪፖርታቸው ÷ በሕይወት የመኖር መብትን ከማክበር፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት እና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር የታዩ ለውጦችን አብራርተዋል።

በዚህ መሰረትም ባለፈው ዓመት ከ729 በላይ እስረኞች በይቅርታና ክስ መቋረጥ መፈታታቸውን አመልክተዋል፡፡

የእስረኞችን መፈታት አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን አውስተው ÷ የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ ለማጠናከርና ሰላማዊ የግጭት አፈታት ሒደትን ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ98 ማረሚያ ቤቶች እና በ649 የፖሊስ ጣቢያዎች ጉብኝት ተደርጓል ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ÷ በክትትሉ መሠረት የታራሚዎች አያያዝ መሻሻሉን አስረድተዋል፡፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታች እና ዴሞክራሲያዊ የድምጽ አሰጣጥ ሒደት እንዲሁም ከፍተኛ የመራጮች ተሳትፎ መመዝገቡ አበረታች መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና በግጭቶች የሚጎዱ ዜጎችን ጥበቃ ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በቤተልሄም መኳንንት