አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ የጋራ ትብብር እና ልማት ቁልፍ ሚና የሚጫወት ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክት ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት አፍሪካውያን መቻላቸውን ያሳየና የጋራ ትብብር የት እንደሚያደርስ መመሰከሪያ ቁልፍ ንብረት ነው፡፡
በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚከሰቱ እንደ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ እና ድርቅ ያሉ ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተደራራቢ ፈተናዎች ለመቋቋም አስተዋፆኦው ከፍተኛ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለትብብር፣ለቀጣናዊ ትስስር እንዲሁም ለዓባይ ውሃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የማይናወጥ አቋሟን ስታሳይ ቆይታለች።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ፥ በሀገራት መካከል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ስትገነባ የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው።
ግድቡ ለቀጣናዊ ልማት፣የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን ለመገንባትና የኢነርጂ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
ግድቡ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተከናወነ ትልቅ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ነው ያሉት አምባሳደሩ፥ የአየር ንብረት ፈተናዎችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችሉ ሰፊ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል ሲሉም አመልክተዋል።
ግብፅ በየጊዜው የምታነሳናቸውን ውንጀላዎች በተግባር ውድቅ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያም በጋራ መልማት በጋራ ማደግ የሚለውን አቋሟን እያራመድ ትገኛለች፡፡
ግድቡ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት፣ በውሃ ማከማቸት እና የጎርፍ አደጋን በመቀነስ ረገድ ለሱዳንና ለግብጽ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም ግብፅ ግን ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› በሚል አጉል ጠብ አጫሪነት ባህሪዋ ኢትዮጵያን በየጊዜው መክሰስዋን አላቆመችም።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ 85 ከመቶ በላይ በምታመነጨው የዓባይ ወንዝ ላይ የልማት ሥራዎችዋን መስራት አላቆመችም ፡፡
የሕዳሴ ግድብ ውሃ የሚገኝበት አካባቢ ከግብጹ አስዋን ግድብ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ትነት ያለው ነው፤ ይህም በትነት ምክንያት የሚባክነውን የውሃ መጠን በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርገዋል።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍሰትን በመቆጣጠር በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ሊደርሱ የሚችሉ የተፈጥሮ አደጋዎችንም የሚቀንስ ፕሮጀክት ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ጽናትና አንድነት እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው የሃይል ትስስርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በእመቤት ሲሳይ