አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታሪክ ምስክር ነው ፤ ኢትዮጵያ የተፈተነችበት ጊዜ ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቷ የወርቅ መለያ ሆኖ አልፏል።
ዛሬ በመደመር መንግሥት ሥር ነቀል ሪፎርም የጎለበተው የመከላከያ ሠራዊት ፣ ጀግንነቱን ከሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ከዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ጋር አጣጥሞ ይዟል።
የኢትዮጵያ ታሪክ ከውጭ ወረራና ከውስጣዊ ፈተናዎች ጋር ተጋፍጦ የማለፍ የብዙ ዘመናት ውጣ ውረዶች የሞሉበት እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል።
በዚህ ረጅም ጉዞ ውስጥ መከላከያ ሠራዊት የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ማረጋገጫ ግንባር ቀደም ምሰሶ ሆኖ ዘልቋል።
የመደመር መንግሥት የጸጥታ ተቋማትን ትውልድ ተሻጋሪነት ለማረጋገጥ ባደረገው ትኩረት፣ የሠራዊቱን የልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የሜካናይዝድ፣ የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር እና የሳይበር ኃይሎች በስር ነቀል የሪፎርም ሥራዎች አጠናክሯል።
ሠራዊቱ በምድርና በባሕር ኃይል አደረጃጀቶች ጭምር በመጎልበት በቀጣናው የማይናወጽ ጠንካራ የኃይል ሚዛን መፍጠር ችሏል።
የዛሬው መከላከያ ሠራዊት በሰው ኃይል ብቃት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ቴክኖሎጂ እና በሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ታላቅ መዋቅራዊ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።
እንደ ሆሚቾ ተተኳሽ ማምረቻ እና ስካይዋርድ ኤሮኖቲክስ ባሉ ሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በሀገር ውስጥ የማምረት፣ የከባድ መሣሪያዎችንና ታንኮችን በሪቨርስ ምህንድስና የማደስ አቅም ተፈጥሯል።
ሎጂስቲክስ የሚያጓዙ ድሮኖች፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚንቀሳቀሱ ተዋጊ ጀቶች፣ እንዲሁም የጠላትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመሰለልና በካሚካዜ ድሮኖች ምሽጎችን የማፍረስ አቅምም ተገንብቷል።
ከሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና ከሳይበር ደኅንነት ጋር የተደረጉ ዘመናዊ ትስስሮች ሠራዊቱ የዘመኑን ወታደራዊ ሥጋቶች በራሱ ዕውቀት ለመመከት የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ብቃትን አጎናጽፈውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሀገራችን ዛሬ ላይ በራሷ ዕውቀትና በልጆቿ አቅም የላቀ የቴክኖሎጂ ብቃት ያላቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖች፣ ዘመናዊ የታጠቁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን፣ ከባድ መሣሪያዎችንና መድፎችን፣ እንዲሁም ተተኳሽ ጥይቶችን በራሷ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ችላለች።
የሠራዊቱ የዘመነ አቅም ሀገርን ከውስጥና ከውጭ ከሚመጡ አደጋዎች ከመጠበቅ አልፎ፣ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ስምሪቶች ተሰማርቶ ለቀጣናዊ ሰላም ሰብአዊና ቁሳዊ መሥዋዕትነት በመክፈል ላይ ይገኛል።
ይህም የኢትዮጵያን አህጉራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የሰላም አምባሳደርነት በአስተማማኝ ሁኔታ አጽንቶታል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ ቴክኖሎጂን ከጀግንነት፣ ሙያዊ ብቃትን ከሀገር ፍቅር ጋር አጣጥሞ የያዘ የኢትዮጵያ ሕያው ጋሻ ነው።
በሶስና አለማየሁ