የሀገር ውስጥ ዜና

ከፉክክር ወደ ትብብር፡ ለብሔራዊ አንድነት

By tigist gizachew

October 10, 2026

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከርና አካታች የፖለቲካ ምህዳርን መፍጠር የሚቻለው የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነቶቻቸውን በማክበር የሀገርን የጋራ ጥቅም በማስቀደምና በኃላፊነት ስሜት በጋራ መሥራት ሲችሉ ነው።

በሀገር ግንባታ ሂደት የፖለቲካ ተቀናቃኝነት የግድ ወደ ጠላትነት መቀየር የለበትም። የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞችና አቋሞች ያሏቸው ወገኖች በሀገራዊ ጥቅሞች ላይ በጋራ ሊሠሩ በሌሎች ጉዳዮች ደግሞ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊወዳደሩ ይችላሉ።

ይህ አካሄድ የፖለቲካ ብስለትን ከማሳየቱም በላይ ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም መሠረት ይጥላል። በተለይም ሉዓላዊነትን፣ ሀገራዊ ጥቅሞችንና የሕዝብን ደኅንነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ ኃይሎች በጋራ መቆማቸው የሀገርን የመቋቋም አቅም ያጠናክራል።

በተመሳሳይ የተለያዩ ማህበረሰቦችና የፖለቲካ ኃይሎች በሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚፈጠር አካታች ምህዳር የመገለል ስሜትን በመቀነስ የዜጎችን የባለቤትነት ስሜት ያጎለብታል።

ሀገር ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚሳተፉባት የጋራ ቤት ናት። በዚህ የጋራ ቤት ውስጥ የሁሉም ወገኖች ድምፅ፣ ፍላጎትና ዕይታ በአግባቡ ካልተወከለ ዘላቂ ሰላምንና ሁሉን አቀፍ ልማትን ማረጋገጥ ይከብዳል። ስለሆነም የሐሳብ ልዩነቶችን በውይይት ማስተናገድና የጋራ መፍትሔዎችን መፈለግ ለሀገር ግንባታ ወሳኝ ናቸው።

ልዩነቶች የግጭት ምንጭ ከመሆን ይልቅ ለውይይትና ለሐሳብ ልውውጥ መነሻ ሊሆኑ ይገባል። በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖሊሲ፣ በልማት አቅጣጫና በአስተዳደር አካሄድ ሊለያዩ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ልዩነት የሀገርን የጋራ ጥቅም ለማስከበር ከሚደረግ ትብብር ሊያግዳቸው አይገባም።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በፓርቲዎች መካከል የትብብርና የውክልና ግንኙነት ጉዳይ የተለመደ ባይሆንም የመደመር እሳቤ ግን ከልዩነት ይልቅ የጋራ አብሮነትን በማጉላት የፖለቲካ ኃይሎች ለሀገራዊ ግቦች በጋራ እንዲሠሩ የሚያበረታታ አቀራረብን ይከተላል።

በዚህ አውድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶር) “ዳርና መሐል” የሚለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ በመሻገር ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ የገለጹት ሐሳብ ይጠቀሳል።

ይሁንና አካታችነት በመርህ ደረጃ ከመገለጽ ባለፈ በተግባር መተርጎምን የሚጠይቅ ሲሆን የፖለቲካ ኃይሎች በውሳኔ ሂደቶች ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማግኘታቸው፣ የሐሳብ ነፃነት መከበሩ እና በሰላማዊ መንገድ የሚገለጽበት ሁኔታ መኖሩና የሕግ የበላይነት መጠበቁ ለትብብር ወሳኝ መሠረቶች ናቸው።

በዚህ መልኩ ትብብርና ፉክክር ተቃራኒ ሳይሆኑ እርስ በርሳቸውን የሚያጠናክሩ የፖለቲካ ሂደቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከርና አካታች የፖለቲካ ምህዳርን መፍጠር የአንድ ወገን ብቻ ኃላፊነት አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገርን ዘላቂ ጥቅም በማስቀደም፣ ልዩነቶችን በውይይት በማስተናገድና የፖለቲካ ትግላቸውን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በማካሄድ የየራሳቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

“ከእኔ መቅደም የሀገር መቅደም ይበልጣል” የሚለውን መርህ በተግባር ማሳየት የሚቻለው በጋራ ጥቅም ላይ በመስማማት ብቻ ሳይሆን ልዩነቶችን በአክብሮት በመቀበልና የሕዝብን ድምፅ በማክበርም ጭምር ነው።

በዚህ መንገድ ትብብርን ከፉክክር ጋር በማጣጣም የተረጋጋች፣ የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊ መሠረቷ የጠነከረ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ ይቻላል።

በትዕግስት ግዛቸው