የሀገር ውስጥ ዜና

ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ የአውሮፕላን በረራ እንደገና በመጀመሩ በጣም ተደስተናል – የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች

By Mikias Ayele

October 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ በጣም ተደስተናል አሉ የበረራ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መንገደኞች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀደም ሲል ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ወደ መቐለ ከተማ በረራ እንደሚጀምር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ዛሬ በይፋ ጀምሯል፡፡

የአገልግሎቱን መጀመር ተከትሎም የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ÷የትራንስፖርት አገልግሎት እንደገና በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና ልማትን ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኛ አቋምና ተግባራዊ ርምጃዎችን በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ በረራ መጀመሩ በክልሉ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያፋጥን ተናግረዋል።

ከአገልሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ አሸናፊ ጸጋዬ  ÷ለሥራ ጉዳይ ወደ መቐለ በሄዱበት ወቅት በረራው በመቋረጡ ምክንያት ለችግር ተዳርገው ቢቆዩም አሁን አገልግሎቱ በመጀመሩ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡

የበረራ አገልግሎቱ መጀመር የትግራይ ሕዝብ ከነበረበት ሁለገብ ችግር እንዲወጣ ከሚያግዙ አስፈላጊ ርምጃዎች አንዱ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የፌደራል መንግሥት አሁን የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንደሚያጸና እምነታቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

አቶ ናትኤል ሰለሞን በበኩላቸው÷ የበረራ አገልግሎቱ ዳግም በመጀመሩ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ መሆኑን በጥቀስ÷ የተጀመረው አበረታች የበረራ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

የበረራ አገልግሎቱ ዳግም በመጀመሩ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገልጸው፤ ይህም ለክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያሉት ደግሞ አቶ ሃድራት ኮት የተባሉ መንገደኛ ናቸው፡፡