አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተከታታይ ሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን አጠናቅቋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በ90 ቀናት ዕቅድ መሰረት የክረምት በጎ ፈቃድ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የቤቶች ግንባታና የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን የማሻሻል ሥራዎች ተከናውነዋል።
በግምገማ መድረኩ ከሕዝቡ የተጣለብንን ኃላፊነት በታማኝነት ለመወጣት የኑሮ ሁኔታና ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ ያመጡ፣ ለቀጣይ ሥራዎቻችንም መሠረት የጣሉ ውጤታማ ተግባራትን መፈጸም መቻላችንን ገምግመናል።
ለአፈጻጸማችን ስኬት መሠረት የሆኑት በከተማችን የተፈጠረው የሥራ ትጋት፣ በታማኝነት የማገልገል ባህል፣ በመደመር መርህ በፍጥነትና በጥራት የመፈጸም ልምድ እንዲሁም ጊዜን ሳናባክን ዕቅድን ወደ ተግባር የመቀየር አቅማችን ናቸው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ሥራዎችን አዲስ የፖለቲካ ባህል በሚፈጥር መልኩ ከመፈጸም ባሻገር፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት በማሻሻልና ውጤትን መሠረት በማድረግ አዳዲስ የአመራር ስምሪቶችን ማከናወን ችለናል ነው ያሉት።
የቤት ችግር ያለባቸውና በልማት ምክንያት ከመኖሪያቸው የተነሱ ዜጎች ንጹሕና የዜጎችን ክብር የሚጠብቁ ቤቶች እንዲያገኙ መሰራቱንም ገልጸዋል፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ለመቀነስ የማዕድ ማጋራት ሥራዎችን አከናውነናል ያሉት ከንቲባዋ፤ በተጨማሪም፣ በክረምት ግንባታ አይከናወንም የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ በመቀየር በርካታ ፕሮጀክቶችን ማከናወን መቻሉን አንስተዋል፡፡
በትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍም አራት ትላልቅ የመኪና ማቆሚያና ተርሚናል ማዕከላትን ወደ ሥራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡
አዳዲስ መንገዶችን፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የውሃ ማስወገጃና የፍሳሽ መስመሮችን በመገንባት የጎርፍ አደጋዎችን ለመቀነስና በሰው ሕይወት ላይ ይደርስ የነበረውን የሞት አደጋ ለመከላከል ተጨባጭ ሥራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡
በክረምት ወቅት የሚኖረውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በሰባት የገበያ ማዕከላት ሰፊ የምርት አቅርቦት ወደ ከተማችን እንዲገባ በማድረግና የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ደረጃ በማሳደግ የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ ሰርተናል ብለዋል፡፡
በሰው ተኮር ልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ማኅበራዊ ፍትሕን ከማስፈን አንጻር ጉልህ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት ከንቲባዋ፤ በተቋማትና በግለሰቦች የሚታዩ የአፈጻጸም ልዩነቶችን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከመሠረቱ ለመፍታት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የሚከናወኑት ሥራዎች ከተቋማት ግንባታ አንጻር ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን ገልጸው፤ የተበታተነ አቅም ራዕይን አያሳካም፤ ሀገርንም አይገነባም ብለዋል።
ሁሉም ሠራተኛ በግልጽ የተለየ የሥራ ድርሻና ተጠያቂነት ኖሮት በመደመር መርህ ተቀናጅቶ የሚሰራበትን አሠራር ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው፤ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም፣ የዜጎችን ክብር የሚጠብቅና ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እንሠራለን ብለዋል፡፡