አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሕገወጡን ቡድን ጨርሶ ለማስወገድ እንታገላለን አሉ የዓዲ ጉዶም ከተማ ነዋሪዎች።
በትላንትናው ዕለት በትግራይ ክልል የአዲ ጉዶም ከተማ ነዋሪዎች በነጻነት ወደ አደባባይ በመውጣት፣ ሕገወጡ ቡድን በህዝቡ ላይ ያደርስ የነበረውን አፋኝ ስርዓት፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እና የልማት በደል በጽኑ ያወገዙበት ሰልፍ አካሂደዋል።
በሰልፉ ላይ የታደሙት የከተማዋ ነዋሪዎች ቡድኑ ላለፉት ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰውን ሰቀቀን እና ስቃይ የከፋ እንደነበር አስረድተዋል።
በዕለቱ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳመለከቱት÷ ሕገወጡ ቡድን ወጣቶችን እና ህጻናትን በግዳጅ ወደ ጦር ሜዳ ወስዶ በመማገድ በትግራይ እናቶች ላይም የማይጠፋ ቁስል ጥሎ አልፏል።
ቡድኑ የራሳቸውን ልጆች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ሰላማዊ ቦታዎች አስቀምጠው የድሃ ልጅ ግን በየበረሃው እንዲረግፍ እና እንዲሰቃይ ማድረጉን ገልጸው ከሞት የተረፉትም ቢሆኑ ከባድ አካል ጉዳተኛ ሆነው የሚጦራቸውን አጥተው በየቦታው ተጥለው እንደሚገኙ በምሬት ተናግረዋል።
ወጣቶች የሕወሓት ቡድን የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳን በመፍራት በየጥሻው እና በየበረሃው ተሸሽገው ያድሩ እንደነበር ገልጸዋል።
ቡድኑ ወጣት እንዳያድግ እና አልምቶ ተጠቃሚ እንዳይሆን ሲሠራ የቆየ አፋኝ ስርዓት እንደነበር ያመለከቱት ነዋሪዎቹ አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል መንግሥት በመምጣታቸው ሰላማዊ ህይወት መኖር በመጀመራቸው ወሰን የለሽ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ነዋሪዎቹ ቡድኑ «ጽምዶ» በሚል የሚደርገው ሀገር የማፍረስ ሴራ አሁንም ሆነ ነገ አጥብቀው እንደሚቃወሙ ተናግረዋል።
በከተማዋ ውስጥ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ በማድረግ ህዝቡ ለእንግልት ዳርጎ እንደነበር ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ጦርነትን ሳይሆን ሰላምን፣ ልማትን እና ብልጽግናን እንደሆነ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ጦርነቱ አብቅቶ ህዝቡ አርሶ እና ነግዶ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች እና ህዝቦች እኩል የሚያድግበት፣ የትግራይ እናቶችም ልጆቻቸውን በሰላም አሳድገው ለወግ ማዕረግ የሚያበቁበት አዲስ የሰላም እና የተስፋ ምዕራፍ መከፈቱን ተናግረዋል።
ይህን አዲሱን ምዕራፍ እውን ለማድረግ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ሕገወጡን ቡድን ጨርሶ ለማስወገድ እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
በዮናስ ጌትነት