የሀገር ውስጥ ዜና

የባህር በር፤ የመበልጸግና የህልውና ጉዳይ

By Hailemaryam Tegegn

October 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራትን ጥንካሬ እና የመበልጸግ አቅም ከሚወስኑ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የባህር በር ባለቤትነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

አብዛኛው የዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴና የሸቀጦች ዝውውር በውቅያኖሶችና በባህሮች ላይ የሚከናወን በመሆኑ፤ ቀጥተኛ መውጫ ማግኘት የትኛውንም ሀገር ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ከፍታ የመምራት ትልቅ አቅም አለው።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር የነበራት ቁርኝት ጥልቅና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ነው።

ነይ እንጓዝ ነይ እንሂድ እየተባባሉ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠና ብዙነሽ በቀለ ያቀነቀኑት የዚሁ ታሪካዊ ትስስር ማሳያ ነው…..

….. አድርገን ማምሻችን ከምጽዋ ከአሰብ ወደባችን በቀይባህር የመርከብ ጉዟችን

ወደ ዳህላክ ወደ ደሴታችን…. የኢትዮጵያና የቀይ ባህር ቁርኝት ከዘፈንም በላይ ነው፡፡

ጥንታዊው የአዱሊስ ወደብ፤ በዘመናዊው ታሪክ የነበሩትም ምጽዋና አሰብ ለአያሌ ኢትዮጵያውያን እንደ ትናንት የቀረቡ ትዝታዎች ናቸው፡፡

በአካባቢው ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኃያላን ተርታ ያስመደቧት የሀገረ መንሥት ታሪኮቿ ማጠንጠኛቸው ከቀይ ባህር ተነጥሎ አይታይም፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የነበራትን የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ለማስጠበቅም የባህር በር ባለቤትነቷ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። ሆኖም ግን በታሪካዊና ፖለቲካዊ አጋጣሚዎች የባህር በሯን ካጣች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከባህር በር መነጠሏ ከፖለቲካዊ ተጽዕኖው ባሻገር በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ለወደብ አገልግሎት ብቻ ለመክፈል ተገድዳለች።

የራሳቸው የባህር በር ያላቸው ሀገራት ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር በቀጥታ የመገናኘት፣ የመሸጥ እና በነጻነት የመሸመት ዕድልን ያገኛሉ።

ይህም ሀገራዊ ምርቶችን በዝቅተኛ የትራንስፖርት ወጪ ለውጭ ገበያ ለማቅረብና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ያስችላል።

የትራንዚትና የማጓጓዣ ወጪዎችን ማስቀረት መቻሉ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከማሳደጉም በላይ፤ የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደርጋል።

በተቃራኒው ባህር በር የሌላቸው ሀገራት ገቢና ወጪ ንግዳቸውን በጎረቤቶቻቸው ወደቦች ላይ የተንጠለጠለ እንዲሆን ይገደዳሉ።

በዚህም የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ ከፍ የሚል ሲሆን፤ የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ ለጎረቤት ሀገራት ፖለቲካዊ ፍላጎትና ሁኔታዎች ምቹ ያደርገዋል።

ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የማምረት፣ የማቅረብና የመበልጸግ አቅም እያላት በወደብ እጦት ምክንያት ኢኮኖሚዋ የሚገባውን ያህል እንዳያድግ ሆኗል።

ወደብ ሳይኖራት ለአህጉሪቱ ሙሉ ተምሳሌት የሆነው ዕድገቷ የሚያስደምም ቢሆንም፤ የባህር በር ቢኖራት ኖሮ ልትደርስበት የምትችለው የብልጽግና ከፍታ የብዙ ዜጎቿ የቁጭት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

ዓባይን ከቁጭት ወደ ኩራትና የብሩህ ተስፋ ምንጭነት የቀየረው ትውልድ፤ የባህር በር ባለቤትነትም በዘመኑ እውን እንዲሆን ይሻል፡፡

ይህንን ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲያዊ ውይይትና አብሮ የመበልጸግ እሳቤን በመከተል ለማሳካት ጥረቶችን ከማድረግ ለአፍታም አልቆመም።

የባህር በር ባለቤትነት ተራ የውሃ አካል ይገባኛል ጥያቄ ሳይሆን፤ የሀገርን መጻኢ እድል፣ ኢኮኖሚያዊ ነጻነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚወስን የህልውና መሠረት ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በመልካም ፈቃዱ