አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን አቅም ይበልጥ የማጠናከር ስራው ባልተቋረጠ የሪፎርም መንገድ ላይ እየተጓዘ ይገኛል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የተቀመጡ ሀገራዊ ግቦችንና ዕቅዶችን በተቀናጀ አሠራር በማሳካት የተሰጠውን ኃላፊነትና ተልዕኮ በከፍተኛ ብቃት እየተወጣ ነው።
የሠራዊቱ ዋና ትኩረት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፣ ህዝብን መጠበቅና የልማት ጉዞዎችን ከዕንቅፋት መከላከል ሲሆን፤ በዚህም ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ የተለያዩ አካባቢዎች መረጋጋት በመፍጠር ህዝቡ ወደ መደበኛ ኑሮው እንዲመለስ አድርጓል።
ዘላቂ ሰላም በወታደራዊ አቅም ብቻ የማይረጋገጥ በመሆኑ ህዝቡ ለሰላም የሚያበረክተውን ሚና ማጠናከር ላይም በስፋት ሰርቷል።
የሠራዊቱን አቅም ከዘመኑ ጋር ለማዛመድ ወደ ዲጂታል አሠራር የማሸጋገር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመታጠቅ፣ የምድርና የአየር ኃይል አቅምን የማሳደግ እንዲሁም የመከላከያ ኢንዱስትሪን በሀገር ውስጥ ምርቶች የማጠናከር ሰፊ ሥራ ውጤት አምጥቷል።
ሠራዊቱ ትኩረቱን የሀገርን ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ላይ አድርጎ፤ የማድረግ አቅም፣ የሰው ኃይል፣ የሥልጠና፣ የመሠረተ ልማት እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ልማት ሥራዎችን ወደተሻለ ደረጃ አሸጋግሯል።
አሁን ላይ የሠራዊቱ ቁመና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በአስተማማኝነት ለመጠበቅ የሚያስችል ደረጃ ላይ ደርሷል።
የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ መከታ የሆነና በዘመናዊ ትጥቆች የተደራጀ አስተማማኝ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል።
ለአብነትም የአየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል በአካል ብቃቱ፣ በፅናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ እውቀቱ የውጊያ አቅጣጫ ቀያሪ ኃይል መሆኑን መጥቀስ ይቻላል።
ይህ ኃይል በአስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ሀገራዊ አደራውን በብቃት በመወጣት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በታማኝነትና በቁርጠኝነት ያስከብራል።
ሠራዊቱን በአደረጃጀት፣ በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች የመገንባት ሂደቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ ደግሞ፤ የጠላት ሴራ እንዳይሳካ የጎላ ሚና ይጫወታል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ