የሀገር ውስጥ ዜና

በአፋር ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ሁለተኛ ዙር ድጋፍ እየተጓጓዘ ነው

By Yonas Getnet

October 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ሁለተኛ ዙር ድጋፍ እየተጓጓዘ ነው አለ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን።

በአፋር ክልል የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወገኖች ሁለተኛ ዙር ድጋፍ ለማድረስ በዛሬው ዕለት ከአዳማ የእህል ማከማቻ ማእከላዊ መጋዘን ሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ስፍራው ተንቀሳቀሰዋል።

ክልሉ በራሱ አቅም ምላሽ ለመስጠት ርብርብ እያደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ በማጠናከር ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በራስ አቅም ምላሽ የመስጠት ጥረቱ የሚቀጥል መሆኑን አመልክቷል።

በመሆኑም በአፋር ክልል የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሹ ወገኖች እየተላከ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚደረግ መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

የመጀመሪያው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ከቀናት በፊት በተመሳሳይ ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መጓጓዙ ይታወቃል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ