አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በህንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ የቴአትር ፌስቲቫል ላይ የኢትዮጵያን ጥንታዊ ስልጣኔ፣ ደማቅ ባህልና የአረንጓዴ ዐሻራን ለዓለም አቀፍ ታዳሚዎች አቅርቧል።
“ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛና የጥንታዊ ስልጣኔ ምድር” በሚል ርዕስ በቀረበው በዚህ ዝግጅት ላይ ድራማ፣ ባህላዊ ዜማዎችና ማራኪ ውዝዋዜዎች ተቀናጅተው የቀረቡ ሲሆን፤ የሃገራችን ፊደላት ፣ የቀን መቁጠሪያና ጥንታዊ እሴቶች ቀርበዋል።
በተጨማሪም ቡድኑ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እና በዩኔስኮ የተመዘገበውን የእርከን እርሻ ጥበብ በማቅረብ ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ የምታከናውነውን አርአያነት ያለው ተግባርና ቁርጠኝነት አጉልቶ አሳይቷል።
የህንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና የጥበብ አፍቃሪዎች የታደሙበት ይህ ዝግጅት በኢትዮጵያና ህንድ መካከል ያለውን የባህል ልውውጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረም ሆኗል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ