አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንንና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የልማት ስትራቴጂዋ አካል በማድረግ እየሠራች ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ትዕግስት ፍስሃ።
ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ልዑክ ከሌሎች ሚኒስትሮች፣ ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ከጌትስ ፋውንዴሽን ከፍተኛ ተወካዮች ጋር በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዙሪያ በተካሄደ የክብ ጠረጴዛ ውይይት ተሳትፈዋል።
ውይይቱ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለአካታች ዕድገትና ለዘላቂ ልማት በሚያግዝ መንገድ እንዲጠቀሙበት የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥና የትብብር መስኮችን ለመለየት ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል።
ወ/ሮ ትዕግስት ፍስሃ በውይይቱ ላይ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንንና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን የልማት ስትራቴጂዋ አካል በማድረግ እየሠራች ነው።
ለዚህም እንደ ማሳያ የኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትንና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲን ማቋቋም መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አፍሪካውያን የሰው ሰራሽ አስተውሎት መፍትሔዎችን በማልማት አቅሟን በመገንባት በሰው ሰራሽ አስተውሎት የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በቀጣናዊ ትስስርና በሕጋዊ ማዕቀፎች ዙሪያ ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ዝግጁነት ማረጋገጣቸውን የሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ ያመለክታል።
የዓለም ባንክና ሌሎች የልማት አጋሮች የኢትዮጵያን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩትና ዩኒቨርሲቲ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ