ቴክ

በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘው የኢትዮጵያ የድንበር ላይ ቁጥጥር አስደናቂ ነው – የናይጄሪያ ወታደራዊ ልዑካን

By Hailemaryam Tegegn

October 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመታገዝ የምታካሂደው የየድንበር ላይ ቁጥጥር አስደናቂ ነው አሉ የናይጄሪያ ጦር ስታፍ ኮሌጅ አባላት፡፡

ከኮሌጁ የተውጣጡ ወታደራዊ ልዑካን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በአፍሪካ ቀዳሚ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ልማት ማዕከል የመሆን ራዕይ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ የቡድኑ አባላት በኢንስቲትዩቱ ባዩት ስራ መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ኢንስቲትዩቱ ለጉምሩክ ኮሚሽን ያለማው ስማርት የድንበር ቁጥጥር ስርዓት በገቢና ወጪ ንግድ ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ስማርት ከተሞችን በመገንባትና ስማርት የፖሊስ ጣቢያዎችን በማቋቋም ወንጀልን ለመከላከል የሰራቸውን ስራዎች እንደ ተሞክሮ በመውሰድ፤ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የጸጥታና ወንጀልን የመከላከል ተግባራቸውን ማዘመን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ተግባራት በተመለከተ ለለዑካኑ ገለጻ ያደረጉት የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች፤ ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ ሳይወሰን ከአፍሪካውያን ጋር በመተባበር ለአህጉሪቱ ዲጂታል ሉዓላዊነት መጠበቅ እንደሚተጋ አረጋግጠዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከጉብኝቱ ጎን ለጎን በቀጣይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡