አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ በኢትዮጵያ ያደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት ያጠናከረ እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በላቀ አመራር ዘርፍ ልምድ እንዲለዋወጡ ያስቻለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ትልቅ የሕዝብ ቁጥር፣ ብዝሃ ብሔር፣ ባህል እና ቋንቋ ያላቸው ሁለት ታላላቅ ሀገራት ሲሆኑ፤ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በሰላም ማስከበር ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
የናይጀሪያ የህዝብ ቁጥር 242 ሚሊየን አካባቢ ሲገመት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም ደግሞ 6ኛ ደረጃ ሲይዝ፤ በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ የህዝብ ቁጥር እንዳላት ይገመታል።
በህዝብ ቁጥር ከአፍሪካ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን የያዙት ሁለቱ ሀገራት ዘመናዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በ1960ዎቹ የተጀመረ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 1961 ኢትዮጵያ በሌጎስ ኤምባሲዋን ከፍታለች፡፡
ከ1960ዎቹ እንስቶ እስካሁን ሁለቱ ሀገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በተጨማሪ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እና በአፍሪካ የጋራ ራዕይ ዙሪያ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ይህን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል፡፡
ውይይቱም በላቀ የአመራር እና ስትራቴጂካዊ ተሞክሮ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን፤ ሁለቱ ሀገራት በአመራር ዘርፍ ያላቸውን ተሞክሮ እንዲጋሩ አስችሏል፡፡
በተመሳሳይ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በአገልግሎት ዘርፎች ያከናወናቸውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምሮች ተመልክተዋል፡፡
ይህም ናይጄሪያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር አብራ ለመሥራትና ተሞክሮ ለመውሰድ ያላትን ፍላጎት ያሳየ ሲሆን፤ በዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር ላይ በጋራ ለመስራት ያስችላል።
ናይጄሪያ በምዕራብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ያላቸው ሀገራት ሲሆኑ፤ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች መገናኘት በአፍሪካ ህብረት እና በሌሎች አህጉራዊ መድረኮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ ይረዳል።
የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሼቲማ በኢትዮጵያ ያደረጉት የሦስት ቀናት ሥራ ጉብኝት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዙሪያ ያሉ የትብብር ማዕቀፎችን ይበልጥ ለማነቃቃት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በሚኪያስ አየለ