አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የልማት ሥራዎችን ለመደገፍና የኅብረተሰቡን ፍላጎት በራስ አቅም ለማሟላት በ2019 ከኅብረተሰብ ተሳትፎ 50 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው አለ የክልሉ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት።
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ወርቁ ያየህ ፥ ከታቀደው 50 ቢሊየን ብር በተጨማሪ በአይነትና በጉልበት 30 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ለማሰባሰብ የልማት እቅድ ተይዟል ብለዋል።
እቅዱን ውጤታማ ለማድረግም በክልሉ ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 250/2018 የፀደቀ የኅብረተሰብ ተሳትፎ አማካሪ ምክር ቤት እና አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ኃላፊው ባለፈው የበጀት ዓመት ከኅብረተሰቡ 14 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊና የአማካሪ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አታላይ ጥላሁን በበኩላቸው የእቅዱን አሠራር በግልጽነት፣ በፍትሃዊነትና በተጠያቂነት መርህ እንዲመራ በማድረግ ጠንካራ የልማት አቅም ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አመልክተዋል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በደሳለኝ ቢራራ