የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘች

By sosina alemayehu

October 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ባዘጋጀው “100 Women Heroes” ዓለም አቀፍ ዕውቅና አገኘች።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት በግብርና፣ በምግብ ሥርዓት እና በገጠር ልማት ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ዕውቅና ለመስጠት ያዘጋጀው “FAO 100 Women Heroes” ዓለም አቀፍ የዕውቅና መርሃ-ግብር በጣሊያን ሮም በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተካሂዷል።

በዚህ መርሃ-ግብር ኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ ሰናይት ገዛኸኝ በግብርና እና ምግብ ሥርዓትን በማጠናከር፣ የገጠር ልማትን በማሳደግ እና የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ይህ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በግብርና እና ምግብ ሥርዓት፣ በገጠር ልማትና በማኅበረሰብ ለውጥ ላይ ያላቸውን ጉልህ ሚና የሚያሳይ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለከታል።

ስኬቱ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ጉልህ ሚና አለው።

ወ/ሮ ሰናይት ገዛኸኝ በጋምቤላ ክልል፣ መንገሽ ወረዳ ኩሚ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፣ የቡና ምርትን እና የእንስሳት እርባታ ኢንተርፕራይዞችን በማቀናጀት ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የግብርና ቢዝነስ የገነቡ ሞዴል ሥራ ፈጣሪና አርሶ አደር ናቸው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ