የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ መገንባት – ኑ የኢትዮጵያን ስልጣኔ አብረን እንገንባ

By Hailemaryam Tegegn

October 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት፤ የራሷ የሚባሉ በርካታ ጥበባትና ሥልጣኔዎችን ይዛ ለዘመናት የቀጣናው ሀያል ሆና የዘለቀች ሀገር ናት፡፡

ቅኝ ግዛትን እምቢኝ ያሉ ልጆቿ በአንድነት ተምመው ሀገራቸውን ከወራሪዎች ተከላክለው በነጻነት በመዝለቃቸው፤ ሀገራችን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆን ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ በእነዚህ ቀደምት የሥልጣኔ አሻራዎች እንዲሁም በሕዝብ አንድነትና ሀገር ወዳድነት በተቀዳጀችው ድል ከነበራት ከፍታ አንጻር፤ በብዙ ወደ ኋላ መቅረቷን ልብ ይሏል፡፡

የመደመር መንግሥት የትናንት ወረቶችን ከዛሬ አቅሞች ጋር በማቀናጀት ለተሻለ ነገ መስራትን መርህ አድርጎ በጠራ የፖሊሲ አቅጣጫ ለትውልድ የሚሻገሩ ግዙፍ የልማት እቅዶችን ተልሞ በጊዜ የለንም መንፈስ እየተጋ ይገኛል፡፡

እነዚህ የልማት ሥራዎች የቅርብ የቅርቡን ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ቀጣይ ትውልዶች አማትሮ ኢትዮጵያዊ ስልጣኔን የማንበር ርዕይን የሰነቁ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የመደመር መንግሥት ምስረታ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ኢትዮጵያ ስልጣኔ ስትገነባ ብቻ ነው፡፡

የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያዊ ስልጣኔን መገንባት የሚቻለው፤ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በወጉ አልምታ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነቷን በዘላቂነት ማረጋገጥ ስትችል መሆኑን በውል ይገነዘባል፡፡

በዚህም የቀደመውን ደማቅ ታሪኳን መሰረት ያደረገ፤ ዘመኑን የዋጀ እውቀትና ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ግዙፍ ኢኮኖሚ የመገንባት ጉዞዋን በሚያስደንቅ ፍጥነት ጀምራለች፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት “አንዱን ጥሎ፤ አንዱን አንጠልጥሎ” ያዘግም የነበረውን የኢኮኖሚ ጉዞ፤ በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በመተካት በፈጣን ሽግግር ላይ ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ እያንዳንዱ ዜጋ ትልቁን ምስል በማለም የሚያደርገውን ንቁ ተሳትፎ ይሻል፤ የሥራ ባህልን በማሳደግ በእጅ ያሉ እድሎች እንዳይባክኑ መትጋትን ይጠይቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፤ አዲሱን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እንገነባለን ስንል ተራ ፉከራ አይደለም፤ ይልቁንም በተግባር የሚገለጥ የትውልድ ቃልኪዳን ነው ብለዋል፡፡

በእርግጥም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ሥልጣኔ መሻት በተግባር እየተገለጠ ስለመሆኑ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገለጡ አስደናቂ የልማት ሥራዎችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለዘመናት በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ኢትዮጵያን ከጥገኝነት ማውጣት ያላስቻለውን የግብርና ስርዓት ከመሰረቱ በመቀየር፤ በበጋ መስኖ በተለይም በስንዴ ልማት አስደናቂ ውጤት መመዝገቡ ለዚህ አይነተኛ አብነት ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት የጠራ የፖሊሲ ፍኖትና በሕዝብ ትብብር የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ገና ከጅምሩ ብዙ ርቀት መጓዝ ችላለች፡፡

እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች ግንባታ መጀመራቸው፤ ከእነዚህ የግብርና ልማት ሥራዎች ጋር ተሰናስለው የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ጉዞ በማፋጠን ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ባለንበት ዘመን የኃያላን ሀገራት ጥንካሬ በዋናነት በቴክኖሎጂ አቅማቸው የሚመዘን እንደመሆኑ፤ በዘርፉ ተከታይ ከመሆን መንገድ ወጥታ እኩል የምትራመድ፤ ደግሞም ቀድማ የምትገኝ ለመሆን እየተጋች ትገኛለች፡፡

የዲጂታል ኢትዮያ 2025 ስትራቴጂን በስኬት ባጠናቀቀች ማግስት፤ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ በበለጠ ቁርጠኝነት በፍጥነት እየተራመደች ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ፤ መብራትም ራትም ከመሆን ባሻገር ሀብቶቻችንን በዋዛ ሳንጠቀም የቆየንበትን ትርክት የሻረ የታሪክ እጥፋት ሆኗል፡፡

ለአብነትም በአፍሪካ ግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ግዙፍ የወርቅ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ የመጪውን ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ አመላካች ናቸው፡፡

በዚህ ግን አያበቃም፤ በአዲሱ የመደመር መንግሥት እነዚህ ትውልድን አሻግረው የሚመለከቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይበልጥ እየተበራከቱ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው፡፡

ይህ የሥልጣኔ ጉዞ ከግብ የሚደርሰው፤ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ዓላማ ሲተጉ ብቻ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንደ ሀገር ሁላችንም ወገባችንን አስረን፤ ስሜታችንን ገርተን፤ ጥሪታችንን ቋጥረን፤ አቅማችንን ሰብስበን ትኩረታችንን በግዙፉ ግባችን ላይ አድርገን አዲስ ኢትዮጵያዊ ስልጣኔ ለመገንባት ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል” ያሉትም ለዚሁ ነው፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በኃይለማርያም ተገኝ