የሀገር ውስጥ ዜና

የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ሀገራት ቅድሚያ በሚሰጧቸው የልማት ዘርፎች መመራት አለበት – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

By sosina alemayehu

October 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ሀገራት ቅድሚያ በሚሰጧቸው የልማት ዘርፎች፣ ጥራትና ፍትሃዊ ተደራሽነት መመራት አለበት አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡

በታይላንድ ባንኮክ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በሰው ሀብት ልማት ላይ ያተኮረ መድረክ ተካሂዷል፡፡

ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በዲጂታል ክህሎት ዘርፍ ጠንካራ መሠረት እየጣለች ትገኛለች።

ለአብነትም ብሔራዊ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፖሊሲ በመቅረጽና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ያከናወነቻቸውን ተግባራት አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እየተገበረች እንደምትገኝ የገለጹ ሲሆን፤ የ5 ሚሊየን ኮደርስ መርሐ ግብር እና የመደመር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ በመድረኩ ላይ አስረድተዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስልጠና የሙከራ ትግበራ መጀመሩንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ የስራ እድል ፈጠራን የሚያፋጥን እንዲሁም የሴቶችና የስደተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ዲጂታል ስርዓት እየተገነባ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የክህሎት ልማት የመንግሥት፣ የስልጠና ተቋማትና የሰራተኞች የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፤ ውጤታማነቱ ከሰልጣኞች ቁጥር ባለፈ ባገኙት ክህሎትና በተፈጠረላቸው የስራ እድል ሊመዘን ይገባል ነው ያሉት፡፡