አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የነበራትን የባሕር በር በፖለቲካ ሴራ ተነጥቃ ከባሕር ተገፍታ የበይ ተመልካች ለመሆን ተገድዳ ትገኛለች።
የመደመር መንግሥት በወሰደው ቁጭት አዘል ውሳኔ ኢትዮጵያ ካላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ እና ቀጣናዊ ሚና እንዲሁም ከህዝብ ቁጥሯ አንጻር የባሕር በር የህልውናዋ ጉዳይ እንደሆነ አስቀምጧል። ይህ ተገቢ የሆነ ጉዳይ የመንግሥትና የህዝቡ ዋና አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድሯል።
ጉዳዩ አጀንዳ ከመሆን ባለፈም ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኝ የሚያስችል መሰረት ተጥሏል። በዚህም ጠንካራ የባሕር ኃይል ማቋቋምን ጨምሮ ከባሕር በር ጉዳይ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግባራት በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ነው።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ የባሕር ኃይል ያቋቋመችው በ1948 ዓ.ም ነበር። ነገር ግን በተቀነባበረ የፖለቲካ ሴራ የተነሳ በተገቢው መንገድ ድምጿን ሳታሰማ የባሕር በሯን መነጠቋን ተከትሎ የባሕር ኃይሉ እንዲፈርስና ለ30 ዓመታት ህልውናው እንዲጠፋ ተደረገ።
ነገር ግን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ልዩ ትኩረት የሰጠው የመደመር መንግሥት ሀገሪቱ የባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት በመወሰን ወደ ተግባር ገብቷል።
በዚህ ርምጃ በአፍሪካ ገናና ስም የነበረውን የባሕር ኃይል ትንሳኤ በ2011 ዓ.ም ዳግም ማረጋገጥ ተችሏል።
የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ያለበት፣ በርካታ ሀገራት የጦር ሰፈር የገነቡበት እንዲሁም የተደራጁ የውሃ ላይ ዘራፊዎች ያሉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይልን ዳግም ማቋቋም የግድ ብሏታል።
ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አውድ አኳያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የባሕር ኃይሏን በጠንካራ አደረጃጀት እየገነባች የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ በመሠረታዊ ባሕረኝነት፣ በማሪን ኮማንዶና ሌሎችም ሥራዎች የተለያዩ የሰው ኃይል ግንባታ ሥራዎችን ሰርታለች።
በዚህም ከየትኛውም የውሃ አካላት ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት በብቃት መመከት የሚችል የባሕር ኃይል እየተገነባ ነው።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ እንደሚሉት፤ ባሕር ኃይሉን ማጠናከርና ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
በዚህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብርና ከየትኛውም የውሃ አካል ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት በብቃት የሚመክት ቁመና እንዲይዝ እየተደረገ ነው።
ባሕር ኃይሉ በልዩ ብቃትና በላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ተልዕኮውን መወጣት እንዲችል ከወዲሁ ጠንካራ አቅሞች ገንብቷል። ተቋሙ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሰው ኃይል አቅሙን በማሳደጉም ሆነ የባህር ኃይል ክፍሎችን በማደራጀትና መሰረተ-ልማትን በማሟላት ረገድ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ