የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አምባሳደር – የኢትዮጵያ አየር መንገድ

By betelhem girma

October 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በ1938 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ በረራውን ከአዲስ አበባ ተነስቶ መዳረሻውን ግብጽ ካይሮ በማድረግ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ይነገራል፡፡

በርካታ ፈተናዎች በነበሩበትና የአህጉሪቱ አብዛኛው ክፍል በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር በነበረበት በዚያ ወቅት ነገን አሻግራ የምታየው ኢትዮጵያ የራሷን አየር መንገድ አቋቁማለች፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንግስና በሰማይ በሚያደርገው የበረራ ስኬት ብቻ የሚገለፅ ሳይሆን፤ ለጥቁር ህዝብ ባለው የኩራትና ፅናት ተምሳሌትነት የሚፀናም ጭምር ነው፡፡

ደቡብ አፍሪካዊ ታላቁ ሰው ኔልሰን ማንዴላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር አውሮፕላን ማብረር እንደሚችል የተማሩበት እና አስተሳሰባቸውን ያስቀየረ ተቋም ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡፡

በወቅቱ በነበረው የባለሙያዎች እጥረት ከጉዞው ሳይገታ፣ የውጪ ሀገራት ባለሙያዎችን ሲጠቀም ቆይቶ ኋላም የራሱን ባለሙያዎች በማፍራት የዕድገት ግስጋሴውን አስቀጥሏል፡፡

በርካታ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛት ስመጥር የሆነው አየር መንገዱ ለደንበኞቹ ከሚሰጠው የአገልግሎት ቅልጥፍና አንጻር ተመራጭና አስተማማኝ ሆኗል፡፡

በተለያዩ የፈተና ጊዜያትም ሳይበገር በፅናት አገልግሎት መስጠቱን ያላቋረጠ የኢትዮጵያ አንዱ መልክ ነው፡፡

ለአብነትም እንደ ኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ያሉ ዓለምን ለከፍተኛ ቀውስ የዳረጉ ክስተቶች በነበሩበት ወቅት ሀገራት ሰራተኞቻቸውን ሲቀንሱና በረራቸውንም ጭምር ሲያቋርጡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጭነቶችን በማመላለስ የፈተናውን ወቅት በብቃት የተወጣ ጠንካራ ተቋም ሆኗል፡፡

በአፍሪካ ቀዳሚውን የጄት አውሮፕላን ያስገባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ይህን በማስቀጠል የመጀመሪያውን የቦይንግና ኤርባስ አውሮፕላኖችን ጥቅም ላይ በማዋል ከአፍሪካ ቀዳሚነቱን ይይዛል፡፡

የአየር መንገዱ ታላቅነት መለኪያ፤ ብዛት ባላቸውና ዘመናዊነትን በተላበሱ አውሮፕላኖች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፤ የሰው ሀብትን በማልማት ረገድ በታዋቂ አቪዬሽን አካዳሚው በሚያፈራቸው ብቁ ተማሪዎችም ጭምር ነው፡፡

አየር መንገዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱ የተለያዩ ኮንፈረንሶችና ለቱሪዝም ዘርፉ መስፋፋት አፍሪካን ከቀሪ ዓለማት ጋር በማስተሳሰር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡

የኢትዮጵያን ዓርማ አንግቦ በዓለም ሰማይ ላይ የሚታየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈተናዎችን እየተሻገረ እና ከዘመኑ ጋር እየዘመነ የኢትዮጵያን ከፍታ ለዓለም ማብሰሩን ቀጥሏል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በቤተልሔም ግርማ