የሀገር ውስጥ ዜና

ህገወጡ ህወሓት ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመሻረክ የማይበጅ ጦርነት አውጇል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  

By emebet sisay

October 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ህገወጡ ህወሓት ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመሻረክ የማይበጅ ጦርነት አውጇል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተፈለገው መንገድ ሳይተገበር የከሸፈው በህገወጡ ህወሓት በኩል በተደረጉ የውል መጣስ ተግባራት ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቁልፍ ይዘት ተኩስ ማቆም፣ ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች መመለስ፣ ትጥቅ መፍታትና ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ (ዲ.ዲ.አር) ፕሮግራምን መተግበር፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ እንዲሁም ለህገ መንግስታዊ ስርዓቱ እውቅና መስጠት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በፌደራል መንግሥት በኩል መደረግ ያለበት ሁሉንም ተግባራት መፈጸሙን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገወጡ ሕወሓት ግን ከስምምነቱ በተቃራኒ ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ መሳሪያ ግዢና ልመና ገብቷል ብለዋል፡፡

አክለውም ህገወጡ ቡድን ትጥቅ መፍታትና ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ ምትክ ወጣቱን ወደ ማደራጀትና አፈሳ መግባቱን እንዲሁም ተፈናቃዮችን እንደማስያዣ በመጠቀም  ወደ ቀዬአቸው እንዳይመለሱ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት ድርሻ የሆነውንና የእነርሱ ድርሻ ያልሆኑትን እንደ አየር መንገድ፣ ቴሌኮምና ባንክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን የመዝጋትና ማፍረስ ህገወጥ ተግባራት መፈፀማቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ሰላም ይሻለናል ብለን መክረናቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ህገወጡ ህወሓት ግን የቀረበለትን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለትና የማይበጅ ጦርነት በማወጁ ምክንያት የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከሽፍ ማደረጉን አብራርተዋል፡፡

በቤተልሔም ግርማ