አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በምርጫ መደበኛ አስተዳደር እስኪመሠረት ድረስ ሕዝቡ አንድነቱንና ተቋማቱን መጠበቅ አለበት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ÷ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን ሀሳብ የሚመርጥበትና የራሱን መሪዎች በምርጫ የሚወስንበት ሰፊ የፖለቲካ ተሳትፎ ሊኖረው እንደሚገባ አስረድተዋል።
ትግራይ የአንድ ድርጅት የግል ንብረት ወይም የተለየ የቁጥጥር ክልል መሆን እንደሌለባት አንስተው ሕዝቡ የተለያዩ ሀሳቦችን በነፃነት የሚያቀርብበትና የሚመርጥበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአካባቢ ልዩነቶችን ተጠቅሞ ሕዝቡን የመከፋፈል አስተሳሰብ ከዚህ በኋላ መደገም እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።
የትግራይ ሕዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ መሥራትና የክልሉን ተቋማት መጠበቅ እንዳለበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝቡ አንድነት መረጋገጥ በመንግሥት በኩል ለሁሉም አካባቢዎች እኩል የልማት ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
በትግራይ ክልል ልማት እንዲመጣና ከሕዝቡ ጋር በመሆን ለመልሶ ግንባታና ለሰላም እንደሚሠሩም ገልጸዋል።