አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ከተመለሱት ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው ተቀባ አየለ፤ ራሱን ጨምሮ 75 ወጣቶች በተሳሳተ መንገድ ወደ ጫካ መግባታቸውን ያስታውሳል።
ቀደም ሲል በጫካ በነበሩበት ወቅት ሕዝቡን ላልተገባ ስቃይ፣ እንግልት እና በደል ሲዳርጉ መቆየታቸውን ጠቅሶ፤ ካለፈው ስህተት ተምረው የሕዝባቸውን ዕንባ ለማበስ እና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል እንደገቡ ተናግሯል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ ጋሻው ወልዴ በበኩሉ÷ በግለሰቦች ግፊት እና ጫና ምክንያት የትግሉ ዓላማ ሳይገባን ለሦስት ዓመት ያህል በጫካ ቆይተናል በማለት የነበረውን ሁነት በጸጸት ገልጿል።
ይህ የተሳሳተ መንገድም የወጣትነት ጊዜያቸውን እንደበላው እና በልማት ተሰማርተው ሃብት ማፍራት እና የሕዝባቸውን ሰላም መጠበቅ ሲገባቸው የገዛ ወገናቸውን በሰላም እጦት መበደላቸውን ተናግሯል።
የጫካው ትግል የሕዝብን ስቃይ ማራዘሚያ፤ የግለሰቦች ጥቅም ማስጠበቂ እና የእርስ በርስ መጠፋፊያ መሆኑን በመረዳት ወደ ሰላም እና ልማት ተመልሰናል ነው ያለው።
በመተማ ወረዳ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባደረጉት የማያቋርጥ ጥረት በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ማኅበረሰቡ የተቀላቀሉ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አስማማው አባተ ናቸው።
በቀጣይም የቀሩ ወጣቶች ወደ ሰላማዊው ሕይወት እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ወጣቶች በንግድ፣ በእርሻ እና በልማት ሥራዎች ላይ የማደራጀት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡