የሀገር ውስጥ ዜና

የትግራይ ህዝብ ወደ ታላቅ የብልጽግና ጉዞ የሚሸጋገርበት አዲስ ምዕራፍ

By tigist gizachew

October 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ ከወንድም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ያለውን ጠንካራ ትስስር ጠብቆ በመቀጠል ለሰላም ለህግ የበላይነትና ለጋራ እድገት በጋራ የመቆም አዲስ ምዕራፍን በይፋ ጀምሯል።

ባለፉት ዓመታት ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የራሱን የስልጣን ፍላጎት ለማስጠበቅ ሲል የትግራይን ህዝብ ለጦርነት እና ለሰላም እጦት ሲዳርገው ቆይቷል።

የፌደራል መንግሥትና የሀገር ሽማግሌዎች የችግሩን አጥፊነት በመገንዘብ በተደጋጋሚ የሰላም እጃቸውን ቢዘረጉም ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን የሰላም ጥሪዎችን መቀበል አልፈለገም፡፡

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን ለሰላምና ለውይይት የተሰጠውን ዕድል በተገቢው መንገድ አልተጠቀመበትም፡፡

የእርቅ፣ የሰላም እና የጋራ ልማት ጥሪ የትግራይ ህዝብ ካለፉት ዓመታት የጦርነት እና የግጭት አዙሪት ወጥቶ ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያስችል ዋናው ቁልፍ ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ቁልፍ ይዘት ተኩስ ማቆም፣ ሁሉንም አይነት አገልግሎቶች መመለስ፣ ትጥቅ መፍታትና ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ህይወት መመለስ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስና ለህገ መንግሥታዊ ስርዓቱ እውቅና መስጠት የሚል ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ፤ በእኛ በኩል መደረግ ያለበትን ሁሉ አድርገናል፤ ህገወጡ የህወሓት ቡድን ግን ትጥቅ ከመፍታት ይልቅ ወደ መሳሪያ ግዢና ልመና ገብቷል ብለዋል፡፡

ትጥቅ በመፍታትና ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ ምትክ ወጣቱን ወደ ማደራጀትና አፈሳ መግባቱን ገልጸው፤ ተፈናቃዮችን እንደ ማስያዣ በመጠቀም ወደቀያቸው እንዳይመለሱ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ህገወጡ የህወሓት ቡድን ምክራችንን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመሻረክ የማይበጅ ጦርነት ማወጁን አስታውሰው፤ በዚህም የተሳሳተ መንገድ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከሽፍ ሆኗል ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሀገራዊ የሰላም ጥሪ ልዩነቶችን በጦር አውድማ ሳይሆን በሰለጠነ ውይይት እና ምክክር በመፍታት፣ የትግራይ ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን ጠንካራ አንድነት መልሶ የሚያረጋግጥበት ታላቅ ዕድል ነው።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ ማህበረሰብ ጦርነት ይብቃ በማለት ከኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ ጋር ማደግ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡

የትግራይ ህዝብ በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች የሚታየውን ፈጣን የልማት እንቅስቃሴ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት በትግራይም ማየት ይፈልጋል።

ይህ አዲስ ምዕራፍ የትግራይ ወጣቶች ለግጭት ማገዶ ከመሆን ወጥተው የፈጠራ፣ የልማት እና የሀገር ግንባታ ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ