አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት ማብራሪያ የሕገ ወጡን ህወሓት ማንነት በደንብ ያጋለጠ ነው አሉ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች፡፡
የመቐለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ገብረሕይወት ሕሉፍ÷ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ምሽት በትግርኛ ቋንቋ ያስተላለፉት መልዕክት የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውና የሚቀበለው ነው ብሏል፡፡
ሕገወጡ ህወሓት ወጣቶች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ያደረገ፣ እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ በድህነትና በኋላቀርነት እንዲቆይ ያደረገ ስብስብ መሆኑንም ተናግሯል፡፡
ሌላኛው የመቐለ ከተማ ነዋሪ መሐሪ ይስፋህ በበኩሉ÷ ቡድኑ የራሱን ሰዎች ብቻ በጥቅም ትስስር በማሰባሰብ ገንዘብ ሲዘርፍ የቆየ እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ያመጣው ልማት የለም ብሏል፡፡
ሕገወጡ ህወሓት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት ከትግራይ ሕዝብ አስተሳሰብና ሥነ ልቦና ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑንም ገልጻል፡፡
ቡድኑ የትግራይ ወጣቶችን ለሞት፣ ለረሀብና ለስደት ዳርጓል ያለችው ሌላኛዋ የመቐለ ከተማ ነዋሪ ደግሞ ገነት ደሳለኝ ናት፡፡
እንደ ወጣቷ ገለጻ÷ ቡድኑ «የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ናቸው» በማለት ወጣቶች ሌላ የፖለቲካ ዕይታ እንዳይኖራቸው በማድረግ በክልሉ ውስጥ ብቸኛ የፖለቲካ ተወካይ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ጠላት እንዳለበት ፕሮፓጋንዳ በመሥራት ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር እንዲጣላና በጥርጣሬ እንዲተያይ ሲያደርግ መቆየቱንም አንስታለች፡፡
በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ያደረጉት ቃለ መጠይቅና የሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ሕዝብ በሙሉ የሚቀበለው ነው ስትል ተናግራለች፡፡