የሀገር ውስጥ ዜና

አስመራን ያኮሰመነው አምባገነን አገዛዝ

By sosina alemayehu

October 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኤርትራ በ1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ በተለያየችበት ወቅት የሻዕቢያ አገዛዝ ኤርትራን “የአፍሪካ ቀንድ ሲንጋፖር” እናደርጋታለን ብሎ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠል ከልማት ይልቅ ጦርነት፣ ከትምህርት ይልቅ ውትድርናን ያስቀደመው አገዛዝ ኤርትራን ሲንጋፖር ከማድረግ ይልቅ በድህነት እና ኋላቀርነት የምትጠቀስ ሀገር አድርጓታል፡፡

አገዛዙ ከልማት ይልቅ ጦረኝነት ላይ ትኩረቱን ማድረጉን የተመለከቱ ፖለቲከኞች ኤርትራ የምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፖር የመሆኗ ተስፋ የጨለመ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልፀዋል፡፡

ኤርትራን ለሶስት አስርት ዓመታት ያስተዳደረው የኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ከዘመኑ ጋር በቀጣናዊ ልማት እና የጋራ እድገት ጋር ተሳስሮ ከመሄድ ይልቅ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር በመተባበር ከራሱ አልፎ የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ውስጥ ከትቷል፡፡

የአስመራው አገዛዝ ለ30 ዓመታት የገነባቸው ሜጋ ፕሮጄክቶች እና መሰረተ ልማቶች የሉም፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት ግብፅ ያስቀመጠችውን ሴራ እና ሌሎች እኩይ የፖለቲካ ሽርክናዎችን ሲፈፅም ቆይቷል፡፡

ኤርትራን ከምስራቅ አፍሪካ ሲንጋፖርነት ወደ ድንጋይ ዘመንነት የቀየረው አገዛዙ የኤርትራ ሕዝብ በሀገሩ እንዳይኖር በማድረግ ለጦርነት፣ ለሞት፣ ለስደት እና ለእንግልት ዳርጓል፡፡

ኤርትራ በአሁኑ ሰዓት ዓለማችን ላይ በጀት የሌላት፣ ፓርላማ የሌላት፣ ሕግና ሕገ-መንግሥት የሌላት፣ የኢኮኖሚ እድገቷ የማይታወቅ እንዲሁም ዜጎቿ በስደትና በድህነት የሚታወቁ ሀገር ሆናለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ቆይታ÷ ከ1940 እስከ 1970 ባሉት ጊዜያት ኤርትራ ከ300 በላይ የተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች እንደነበሯት አስታውሰዋል።

ከአፍሪካ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ አካባቢዎች አንዱ ተደርጋ ትወሰድ የነበረችው ኤርትራ በአገዛዙ ምክንያት ባዶዋን ቀርታለች።

ምጽዋ እና አሰብ የመሳሰሉ ከተሞች ያበቡ፣ ያሸበረቁና ዘመናዊ አገልግሎቶች የተሟሉላቸው የነበሩ ሲሆን በወቅቱ በአፍሪካ ቅንጡ እና ለመዝናኛነት የሚመረጡ ከተሞች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ ከተሞቿ ወደኋላ ተንሸራትተው መንደር ሆነዋል። ከ30 ዓመታት በፊት ትልቅ የነበረችው አስመራ ከተማ ዛሬ ከአርባ ምንጭ እና ጅግጅጋ ከተሞች ያነሰች ሆናለች።

ምጽዋ እና አሰብም በርካታ ጎብኚዎቻቸውን አጥተው ሰው አልባ ከተማ ሆነዋል፡፡

የኤርትራ አገዛዝ ልማትና ተቋማትን መገንባቱን ትቶ የኢትዮጵያ ጠላቶች መሳሪያ በመሆኑ፤ ሥራ ወዳድና እንግዳ ተቀባይ የነበረው የኤርትራ ሕዝብ ዛሬ ስደትና እንግልት መገለጫው ሆኗል።

የመደመር እሳቤ መሰረታዊ መርህ «ብቻን መበልጸግ አይቻልም» የሚል ነው። መደመር የአንድ ጎረቤት ሀገር አለመረጋጋት ወይም ድህነት በቀጥታ በሌላው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር በመገንዘብ፣ የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት ቀጣናዊ ትብብርን ያበረታታል።

ኤርትራ የምስራቅ አፍሪካዋን መሪ ሀገር ኢትዮጵያ ድጋፍ እና ትብብር ካላገኘች ካለችበት የድንጋይ ዘመን እንደማትወጣ እሙን ነው፡፡

በመሆኑም ኤርትራውያን ከቀጣናዊ እድገት ትሩፋት ያራቀቸውን አምባገነን አገዛዝ በመታገል ሀገራቸውን ወደ ተስፋ ሊመልሱ፣ እንዲሁም ወጣቶችን ከስደት እና እንግልት ሊታደጉ ይገባል፡፡

በሚኪያስ አየለ