የሀገር ውስጥ ዜና

ነገረ ግርምቢጥ

By sosina alemayehu

October 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለትግራይ ህዝብ መብት እታገላለው በሚው ሕገ ወጡ ህወሓት እና የክልሉን ህዝብ ሰላም እና መረጋጋት በሚያውኩ ድርጊቶቹ መካለል ያለውን ተገላቢጦሽ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲያብራሩ ቡድኑ ሥራው ሁሉ ግርምቢጥ ነው ብለዋል፡፡

ሕገ ወጡ ህወሓት ራሱን የትግራይ ህዝብ መብት ተሟጋች እና ተቆርቋሪ አድርጎ ቢያቀርብም፣ ድርጊቶቹ የሚናገረው ግን በተቃራኒው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለደህንነት ስጋት ለመሰረተ ልማት ውድመት እና በክልሉ ስር ለሰደደ ቀውስ ምክንያት መሆኑን ነው።

ቡድኑ የፖለቲካ መሠረቱን የገነባው በትግራይ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና የመብት ትግል ትርክት ላይ ይሁን እንጂ፣ ፖለቲካዊ ግቡ ከህዝብ ጥያቄ እና ፍላጎት ያፈነገጠ ለጥቂቶች የስልጣን ህልውና ማስቀጠያ ብቻ በመሆኑ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥሏል፡፡

የህዝብን ጥቅም እናስከብራለን በሚል ከመፈክር ባልዘለለ መደለያ ህዝብን ሲያታልል ወጣቶችን አስገድዶ ላላመኑበት ጦርነት ሲማግድ በዜጎች መካከል ልዩነትን ሲዘራ ግጭቶችን ሲቀሰቅስ ቆይቷል፡፡

ለህዝብ እቆረቆራለሁ የሚል ቡድን ቅድሚያ የሚሰጠው ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለመሠረተ ልማት ጥበቃ እና ማህበራዊ ደህንነት መሆኑ ቀርቶ ሕገ ወጡ ህወሓት በሚያደርጋቸው ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ሳቢያ በሚነሱ የጸጥታ ችግሮች ትግራይ ከግጭት ዑደት እንዳትወጣ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዋ እንዲታጎል፣ ኢኮኖሚዋ ከባድ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል።

የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና የመጓጓዣ አገልግሎቶች በአግባቡ እንዳካሄዱ የንግድ ሰንሰለቶች እንዲቋረጡ መሆናቸው ንግግሩ እና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተገላቢጦሽ መሆናቸውን ያሳያል።

ያቀጣጠለው የግጭት እሳት ባስከተለው መዘዝ የሺዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ አካላዊ እና ስነ-ልቡናዊ ጉዳት አድርሷል፤ ንብረት አውድሟል፤ በርካቶችን ለስደት ለምግብ እጥረት፣ ለህክምና እጦት በጥቅሉ ለተደራራቢ ስቃይ ዳርጓል።

ሕገ ወጡ ህወሓት በክልሉ ዴሞክራሲያዊ አሰራርንና የሃሳብ ነጻነትን ከማጠናከር ይልቅ፣ እያካሄደ ያለው የስልጣን ሽኩቻና ህዝብን መከፋፈል የክልሉን ሁለንተናዊ ቁመና አዳክሞታል።

ይህም ቡድኑን ከፌዴራል መንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ መጠቀሚያ ካደረገው ከራሱ ህዝብ ፍላጎት ጋርም አጋጭቶ ድጋፍ አሳጥቶታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘይቤያዊ አገላለጽም በቡድኑ የፖለቲካ አካሄድ ውስጥ ያለውን ትልቅ ተቃርኖ በሚገባ  ያሳየ ነው።

ይኸውም ሕገ ወጡ ህወሓት ለክልሉ ህዝብ በንግግር የሚገባው የተስፋ ቃልና በተግባር የሚመጣው ጦስ ለትግራይ ህዝብ ትልቅ ፈተና ሆኗል።

የተባለውንና የተደረገውን ለማጣጣም ተጠያቂነትን ማስፈን እንዲሁም የህዝብን ሰላም ከቡድን ፍላጎት ማስቀደም ወሳኝ መሆኑን ነው።