አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በስፖርት መሰረተ ልማት በተመዘገቡ አስደናቂ ውጤቶች ለዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ተመራጭ ከተማ እየሆነች ነው፡፡
የከተማ ልማት ለዜጎች ጤናማ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ ሕይወት ለመኖር የሚያስችሉ አካባቢዎችን መፍጠርን ይጨምራል።
ስፖርት ለወጣቶች አቅም ማዳበር፣ ለማኅበራዊ አንድነትና ለማኅበረሰብ ጤና ወሳኝ ሚና አለው።
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በብዙ ሰፈሮች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ባለመኖራቸው፣ ሕፃናትና ወጣቶች በመኪና መንገዶች ላይ ኳስ ለመጫወት ይገደዱ ነበር። ህፃናትም ወተው የሚጫወቱበት ባለመኖሩ ለተለያዩ ማህበራዊ ጫናዎች ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ሆኖ ነበር።
ለመዝናኛና ለጤናማ እንቅስቃሴ መዋል የሚገባቸው ክፍት ቦታዎች ብዙ ጊዜ ለህንፃ ግንባታ ለባለሃብቶች ይሰጡ ነበር፥ ለቆሻሻ ማከማቻነትና ለጤና አደጋ አጋላጭ ሆነው ቆይተዋል።
ዛሬ ግን እነዚህን ተግዳሮቶች ወደ ዕድል በመቀየር፣ ክፍት ቦታዎችን ወደ ስፖርትና መዝናኛ ስፍራዎች የመቀየር፣ ለወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ የስፖርት አማራጭ የመፍጠርና፣ የነበሩ ጥቂት ቦታዎችን ለስፖርታዊ እንቅስባሴ ምቹ እንዲሆኑ አስፈላጊ መሠረተ ልማት በማሟላት የከተማዋን ገጽታ የማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።በዚህም ውጤት ተገኝቷል።
ይህ ለውጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የልማት ራዕይን ወደ ተግባር ከመቀየር ጋር ተያይዞ፣ ከተማዋ ዘመናዊና ለነዋሪዎቿ ምቹ ገጽታ እንዲኖራት እያገዘ ይገኛል።
ከዚህ አንጻርም አዲስ አበባ ያሏትን የስፖርት ማዘውተሪያዎች ቁጥር ማሳደግ ችላለች፣ በዚህ በያዝነው ዓመትም 150 አዳዲስ ስፍራዎችን ለመገንባት ሥራ ተጀምሯል።
ይህ ተነሳሽነት የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ከማስፋት ባለፈ፣ የወጣቶችን ተሰጥኦ ለማዳበርና የከተማዋን የስፖርት ዘርፍ አቅም ለማጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
እነዚህ ሥራዎች አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮችን ለመዘጋጀትና የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን ያላትን አቅም እያጠናከሩ ነው። በስፖርት ዘርፍ የተያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ የከተማው አስተዳደር፣ የስፖርት ቤተሰቡ፣ የግሉ ዘርፍና መላው ማኅበረሰብ በጋራ መረባረብን ይጠይቃል።
ሁላችንም ተባብረን ሀላፊነታችንን በመወጣት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና አበባ፣ ለዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ተመራጭና መዳረሻ የሆነች ከተማ እናድርጋት፡፡