የሀገር ውስጥ ዜና

የቀይ ባህር ታሪካዊ እውነት፤ ከዘመናት አብሮነት እስከ ሻዕቢያ የጥፋት ሴራ

By Yonas Getnet

October 21, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና የኤርትራ ታሪካዊ ቁርኝት በዘመናት የተሸመነ፣ በደም፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በሥነልቦና እሴቶች የተገነባ ውህድ የጋራ ታሪክ ነው። የዛሬዋ ኤርትራ በታሪክ ማህደር የኢትዮጵያ ጥንታዊ የስነመንግሥት አካል ነበረች።

ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት ታሪክ ተጋርተው የኖሩ ሲሆን፤ የኢኮኖሚና የስልጣኔ ማጠንጠኛው በቀይ ባህር እና አካባቢው ላይ የተመሰረተ ነበር። የኢትዮጵያ ነገስታትና ባህረ ነጋሾች ህዝቡን አስተባብረው የውጭ ወራሪዎችን በመመከት የከፈሉት ውድ መስዋዕትነት ለትውልድ ተላልፏል።

በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሴራ በኋላም በወራሪው ጣሊያን አማካኝነት የቀይ ባህር ግዛት ከእናት ሀገሩ መነጠሉ ለጂኦፖለቲካዊ ቀውስ መነሻ ሆነ። ይህ ታሪካዊ በደል የኤርትራን ህዝብ ከኢትዮጵያ ከመለያየቱም በላይ በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጠሩ የፖለቲካ ልሂቃን የተዛባ የታሪክ ትርክት እንዲያራምዱ በር ከፍቷል።

የውጭ ኃይሎች በተለይም ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህንን ክፍተት በመጠቀም ጀብሃን በኋላም  ሻዕቢያን በማደራጀት ኢትዮጵያን ከባህር በር ለማራቅና በቀጣናው ዘላቂ አለመረጋጋት ለመፍጠር ሰሩ።  የኤርትራ ነፃነት ግንባር (ጀብሃ) አመሰራረት እና የደጋፊ ሀገራት ማንነት ይህን የሚያሳይ ነው፡፡

በአረብ ብሔረተኝነት እና በሶሻሊዝም አስተሳሰቦች የተቃኘው ጀብሃ አብዛኛውን የገንዘብና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ያገኝ የነበረው ከግብፅ፣ ሶሪያ እና ኢራቅ  ነበር። በተለይ ግብፅ ለቡድኑ ካይሮ ላይ የሬድዮ ጣቢያ በማቋቋም ጭምር ጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳ እንዲያሰራጭ እገዛ ስታደርግ ቆታለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የውስጥ ባንዳዎች ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሻረክ ኢትዮጵያን በማዳከም ኤርትራ በድጋሜ እንድትነጠል እና የኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ አድርገዋል።

ከዚህ ሕገ ወጥ እና የግፍ ተግባር በኋላም የሻዕቢያ መንግሥት ሀገሪቱን ለቀጠናዊ ውዝግብና ለጥፋት አጀንዳዎች ማስፈጸሚያነት አውሏታል።

የኢትዮጵያን ሕጋዊና ታሪካዊ የባህር በር ጥያቄ እንደ ሀገራዊና ቀጠናዊ ስጋት በመቁጠር ከግብጽና ከመሰል ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመተባበር የጥፋት ተግባሩን ቀጥሏል።

ሻዕቢያ  የውስጥ ቀውሱን እና የኢኮኖሚ ድቀቱን ለመሸፈን ሲል የኢትዮጵያን ጠላቶች በማሰባሰብ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የሚያደርገው ይህ መፍጨርጨሩ ስርዓቱን የማሰንበት ሙከራ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪክም ሆነ በሕግ ያላት የባህር በር ፍላጎት የሉዓላዊነትና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሊገታው የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል አይኖርም።

የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የዘመናት አብሮነት ታሪክ የጥፋት ኃይሎች ከሚያራምዱት ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርክት በላይ የጸና በመሆኑ የወደፊቱ ዕጣ ፈንታቸውን በጋራ ሊገነቡት ይገባል።

የቀጣናው ህዝቦች የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለውም የዚህን እውነተኛ የታሪክ መሠረት በመረዳትና የጋራ የትብብር መንገዶችን በቁርጠኝነት በመከተል ብቻ ነው።

በዮናስ ጌትነት