የሀገር ውስጥ ዜና

ፈተናዎችን በድል ለመወጣት አንድነትን ይበልጥ ማጠናከር ይገባል- አቶ ጌታቸው ረዳ

By sosina alemayehu

October 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚገጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር የውስጥ አንድነት እና የመከላከያ አቅምን ማጠናከር ይገባል አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ።

አቶ ጌታቸው ይህንን ያሉት በኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ እና በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት “ኅብረት ወይስ ክህደት? ፀረ ኢትዮጵያ ጥምረት ከየት ወዴት” በሚል መሪ ሀሳብ በብሔራዊ መከላከያ ኮሌጅ በተዘጋጀ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

የሀገራችን ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ እና የውኃ ሀብታችን በታሪካዊ ጠላቶቻችን የትኩረት ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል ያሉት አቶ ጌታቸው፤ እነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚፈልጉትን ዓላማ ለማስፈፀም የውስጥ ድክመቶችን እንደሚጠቀሙ አንስተዋል፡፡

በተለይም እንደ ግብፅ እና ኤርትራ ያሉ የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የማይሹ አካላት ዓላማቸውን ለማስፈፀም ሕገ-ወጡን ህወሐት እና ሌሎች ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድኖችን እንደሚጠቀሙና በሀገር ውስጥ ለሚፈጠር ግጭት ለቡድኖቹ የጦር መሳሪያ እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያቀርቡ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ የጂኦፖለቲካ አቀማመጥ እና ያላት የተፈጥሮ ፀጋ ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ እንዳደረጋት ገልጸው፤ በየጊዜው የሚገጥሙ ችግሮችን እያሸነፉ ለመሻገር የውስጥ አንድነት እና የመከላከያ አቅምን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ “ፀረ መንግሥት” እና “ፀረ ህልውና”ን የመለየት ችግር እንዳለ ጠቁመው፤ የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከት ሁኔታ የውስጥ ባንዳዎችም በየዘመኑ ይተባበራሉ ብለዋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በድል ለመሻገር የውስጥ አንድነቷን ማጠናከር፣ የወታደራዊና ደህንነት አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡